Uncategorized

“በአባቶቻችን ትልቅ ነበርን …!”

ምንም የማያውቁ የነገ ሃገር ተረካቢ ህፃናት መርጠው ባልተወለዱበት ዘራቸው ምክንያት እየተሸማቀቁ በውስጣቸው የጥላቻና አግላይነት ስሜትን ይዘው በማደግ ነገ ዛሬ እንደምናየው ሁሉ ክርስቶስ በአምሳሉ የሰራውን ቤተመቅደስ (ሰው) ዘቅዝቀው የሚሰቅሉ፣ በድንጋይ ቀጥቅጠው የሚገሉ፣ እንደአውሬ በቀስት የሚያሳድዱ፣ የብሔር ታርጋን እያነበቡ የሚያፈናቅሉ፣ የሃይማኖት ተቋማትን የሚያቃጥሉ፣ አባቶቻቸውን በጠረባ የሚማቱ፣ ሴት እህቶቻቸውንና ህፃናትን የሚደፍሩ፣ የሰዶምና ገሞራን ታሪክ ዘንግተው የፆታ አጋርን ስለማግባት መብት በአደባባይ የሚከራከሩ፣ “ይህን ያህል እንቶኔዎችን አፈናቀልን፣ ገደልን፣ አቃጠልን!” በሚል ፅዋ የሚጠጡ ህሊና ቢስ አውሬዎች የፈሉባት ሃገር ስትሆን ከማየት በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር ይኖራል፡፡
ትላንት ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር የረባ ነገር ላንፈጥር የከፈልነውን ዋጋ ረስተን ዛሬ በብሔር ተቧድነን ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ዋጋ ለመክፈልና ትውልድን ዋጋ ለማስከፈል የምንሰራ …ዛሬ የምናደርገው ነገር ነገ ይዞት ስለሚመጣው ጣጣ የማናስብ …ግብ የሌለን …ድንጋይ ደርድረን በዘጋነው መንገድ የራሳችንን ዜጎች የምናስርብና ከህክምና የምናግድ …ለራሳችን ስራ ፈተን የዚህችን ድሃ ሃገር መንግስት ስራ የምናስፈታ …ያልሰለጠነ ድጋፋችንም ሆነ ተቃውሟችን ሁሌም መልሶ እኛኑ ዋጋ የሚያስከፍለን …በህዝብም በመሪም ያልታደልን፣ መሪ እንዲወጣልንም የማንፈቅድ…እንደ የኑሮ ውድነት፣ ስራ-አጥነት፣ ልመና፣ የጎዳና ህይወት እና የፆታ ተዳዳሪነት ያሉ ማህበራዊ ቀውሶች መንስኤም ገፈት ቀማሽም የሆንን …አንዱ የሰራውን በሌላው የምናስፈርስ …በዜሮ ድምር አዙሪት ውስጥ ሁሌም ዋጋ እንድንከፍል የተፈረደብን የድህነት ጋሻጃግሬዎች ሆነናል፡፡
አባቶቻችን በሰሯቸው ዓለምን ጉድ ያስባሉ ታሪኮችና ትርክቶች ቆዳችንን የወጠርን የታሪክ ሃብታሞች መሆናችን ይብቃና እስቲ የራሳችንን ታሪክ እንስራ!
~~~~~~~~
ጥቂቶች የሆዳችን ቀፈት እስኪገለበጥ እየበላን “ገደል ትግባ!” የምንላትን ሃገር ለማቅናት እልፎች በምንም የማይተካ ዋጋ ከፍለዋል …ዛሬ በየቤተ-እምነቱ፣ በየገዳማቱ እና አድባራቱ ባህታውያን አባቶችቻችንና ደናግላን እናቶቻችን ዓይናቸው እስኪጠፋ የሚያነቡት …ቆሎ እየቆረጠሙ ስጋቸው እስኪዝል የሚፆሙትና የሚፀልዩት ከሞት በኋላ ስላለው ዘላለማዊ ህይወታቸው ብቻ ተጨንቀው እንዳይመስለን …ስለዚህች እኛ አፋችንን ሞልተን “ገደል ትግባ!” ስለምንላት (በተግባርም ወደገደል እየገፋናት ስላለችው) አሜኬላ ስለበዛባት አሳዛኝ ምድርም ጭምር እንጂ!
እነሱን የሚያሳስባቸው እኛን የሚያሳስበን የበላይነት ስሜት፣ ኃያልነት፣ ሃብት፣ ሌላን ጨቁኖና ከሌላ ነጥቆ ሁሉንም የራስ የማድረግ ዘመንኛ ፈንገስ /በሽታ/ አይደለም፡፡ እነሱን ሰላም የሚነሳቸው የእኛ ሰላም ማጣት የእኛ ደህንነት ነው…እነሱን የሚያንገበግባቸው ልጇ እንደወጣ የሚቀርባት የሃገሬ ወላድ እናት ለቅሶ ነው፡፡ …እነሱን የሚያስጨንቃቸው ዓለምን ያስደመሙ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ተፈጥሮኣዊ ሃብቶች እና ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ባለቤት የሆነች፣ ቀደምት አባቶቻችን ዘር ሳይቆጥሩ የፀጉሯን ዘለላ አናስነካም ብለው የደምና አጥንት ዋጋ ከፍለው የገነቧት፣ በቅዱሳን መፅሐፍት ስሟ በተደጋጋሚ የተጠራችው ቅድስት ሃገራችን …ትላንት የዓለም ፖለቲካና ሃያላን መንግስታት ጠፍጥፈው እንደሰሯቸው አንዳንድ ጨቅላ ሃገራት በሆያሆዬ ለመፈረካከስ ጫፍ መድረሷ ነው፡፡
እነሱን የሚያስነባቸው የጌታችንን እናት ከግብፅ በረሃ የተቀበለች …ነብዩ መሃመድ “ሰው በእምነቱ ወደማይጎሳቆልባት እና ፍትሃዊ ንጉስ ወዳለባት ሃበሻዋ ምድር ሂዱ!” በማለት ወደኢትዮጵያ የላኳቸውን በእምነታቸው አረቦች ሲያሳድዷቸው የነበሩ ተከታዮቻቸውን የተቀበለች …ስንቱን ያስጠለለች ሃገር ዛሬ ዜጎቿ በብሔር ተቧድነው እርስ በርስ የሚፈናቀሉባት …እንደ ሶሪያ፣ የመን እና ኢራቅ ለገዛ ዜጎቿ ጩኸት መድረስ አለያም እንደሱማሊያና ደቡብ ሱዳን ካሉ ጎረቤቶቿ መጥፎ ታሪክ መማር ተስኗት ራሷን ለውድቀት ስታዘጋጅ ማየታቸው ነው፡፡
~~~~~~~~
አምላክ ሆይ! ትምቢትህ ይፈፀም ዘንድ ግድ እንደሆነ እናምናለን …ግና በዓለም ላይ ያሉ እምነት የለሽ ህዝቦች አንተ ላይ እየተዘባበቱ ሳይቀር ምድራቸው የሰላምና የፍሰሃ ሆኖ እያየን በየእምነት ተቋማቱ፣ በየአድባራቱና ገዳማቱ ሌት ተቀን ስምህን እያነሱ የሚያነቡ ህዝቦች ላይ ይህ ሁሉ ፈተና ለምን? … ይህች ቅድስት ምድር ጊዮን ዓለም የሌለው ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ተፈጥሮኣዊ ሃብት ተሸክማ ህዝቦቿን መመገብ ተስኗት መኖሯስ ምን ያህል ፍትሃዊ ነው?
~~~~~~~~
ወንድሜ “ለዓመታት የተዘራብን ዘር!” ምናምን እያልን ራሳችንን አናታል፡፡ ምድር እኮ አሜኬላን ከንፁህ ዘር ጋር ማብቀል የጀመረችው ተረግማ ነው …ያም ሆኖ ግን ገበሬው መልካም ፍሬን በዘራና ማሳውን በተንከባከበው ልክ መልካም ፍሬን ይሰበስባል፡፡ እኔና አንተ ሰው ነን …ማገናዘብ የምንችል፡፡ ከየት እንደመጣ የማናውቀውን እግዚዚያብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው የመጥላት ዘመቻ ከምንቀላቀል ጎረቤታችን እንደ ወላጅ ተቆጣጥረው ያሳደጉንንና ለስኬት ያበቁንን የሌላ ብሔር ተወላጆች እናስብ፡፡ …እነሱን መጥላት ይቻለናልን? …ከሆነ ይህ እርግማን ነው! …ሌሎች በእኛ ላይ የሚዘሩብንን የጥላቻ ዘር አምክነን በምትኩ ፍቅርን እናብቅል …ያኔ ለሃገራችን የራሳችንን አንድ ታሪክ ሰራን እንላለን፡፡
እናም ሁሉም ነገር ከሃገር በታች ነው …ሃገር ስትኖር ሁሉም ይኖራልና ሃገራችንን እናስቀድም …ዛሬ ስለበዛን አለያም ጩኸታችን ስለደመቀ ያሸነፍን እንዳይመስለን እንጠንቀቅ …እናድብ! …አሸናፊዎች የምንሆነው በብሔር የምናደራጀው መንጋ ስለበዛ ሳይሆን እንደሃገር ስንደራጅና ስናሸንፍ ብቻ ነውና!

Aschalew /የአማረች ልጅ/

Categories: Uncategorized

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s