ፖለቲካ

” አ ስ ታ ር ቁ ን “(በፋንታሁን ዋቄ)

ኢትዮጵያኖችን ከእብደት ጠርቶ የማስታረቅ ኃላፊነታችሁን ተወጡ:: ለጳጳሳት፣ ለካህናት፤ ለሸኾች፣ ዑስታዞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሣ መሪዎች፣ የዘረኝነት ደዊ ያልለከፋችሁ የዩኒቭረሲቲ ፕሮፌሰሮች ሁሉ፡-

ተቆንጥጦ ያላደገ ልጅ ጉልበት ሲያወጣ ወልደው ያሳደጉትን ወላጆቹን አንደሚዳፈር በሐገራዊ እውቀት፣ ጥበብ፣ አስተዳደርና ፍልስፍና ሳይበለጽጉ ላለፉት 100 ዓመታት ከውጭ በተቀዳ ባዕድ ትምህርተት የደነቆረው ትውልድ ወደ ፍጹም እብደት ደርሶ እናት ሀገሩን እየተዳፈረ ይገኛል፡፡

ይህ ትውልድ እውነተኛ ሀገራዊ ሰው የመሆንና የመኖር ትርጉምን፣ እውነተኛ ታሪክን የሚማርበት እድል ተነፍጎታል፤ በተቃራኒው የታሪክ ትምህርትና ትርጓሜ የሚሰጠው ግልብ በሆነ የባዕድ ትምህርት ማያቸው በተባለሹ ከእውነት ይልቅ ለፖለቲካ ርዕዮተዓለም ታማኝ በሆኑ ካድሬዎችና የፖለቲካ ሰባኪዎች(አክቲቪስቶ) ነው፡፡

የሰው ልጅ ምንነትና ማንነት የሚበየነው በኢኮኖሚያዊ ጥቅምና በሆድ ደረጃ ብቻ ነወው፤ የሰው መንፈሳዊና ባህላዊ ክብሩ ተዘንግቶአል፤ ኢትዮጵያዊያን እንደ ምርት ግብአት፣ እንደ ኢኮኖሚ ማሽን፣ አንደ ጦር መሣሪያ በሚቆጥሩት የጎሣ ፖለቲከኞች እጅ ተይዟል፤ ወደ ራሱ ተመልሶ ከወገኒ አንዳይ ታረቅ ገዥዎችና የሚዲያ ጀግኖች አጨልመውበታል፡፡

የፍትህና የእስተዳደር ሥርዓት ትርጉም የሚያገኘው በብልጥና ጉልበተኛ ልጆች አመራር ሥር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሰው በጎሣና በታሪካዊ ልዩነቶች እየተፈረጀ እኛና እነርሱ በመባባል አንዱ በሌላው ላይ የጠላትነት እንቅስቃሴ በማድረግ ሰውን እንደ በግ ሲያሳርድና ሲያሳድድ፣ ሕፃናትን በቡድን ሲያስደፍር፣ ጎረቤትን በቆንጭራ ሲያስቆርጥ (ቡራዩን፣ በሻሻ፣ አወዳይን፣ ጅጅጋ፣ ቀይና ነጭ ሽብር፣ በእር ቤት ጥፍር ነቀላና ሶዶም መፈጸም ወዘተ እንደ ምሳሌ እንመልከት) ብዙ አሥርት ዓመታት እያሳለፍን ነው፡፡

በየቤተእምነቱን ሰርገው የገቡ የፖለቲካ ሠራተኞች ሃይማኖት ከፈጣሪ ጋር የሚገናኙበት፣ ራስን ከሀሰትና ከክፋት የሚጠብቁበት፣ ሆድና ፍተወትና ድል የሚነሱበት፣ ለሌላ ሰው የሚኖርበት መሆኑ ቀርቶ ቡድን የሚደራጅበት፣ አንዱ ሌላውን ከምጣኔ ሀብትና ከሀገራዊ ተሳትፎ ለማግለል የሚደራጅበት መሰባሰቢያ ሆኗል፤ የሀገር ልጆች አጠገባቸው ከቆመው ወንድማቸው በበለጠ በእምነትና በሀሳብ ይቀርበኛል፣ ርእዮተ ዓለሜን ይደግፍልኛል ከሚለው የባሕር ማዶ ባዕድ ጋር ተባብሩ ጎረቤቶን የሚያጠቃበት የሀሰት አውድ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

ጥሪዬ ከዚህ ሁሉ ዘመናዊ ድንቁርና አምልጣችሁ፣ በባህላችሁና በእምነታችሁ ጸንታችሁ ላላችሁ የባህል፣ የእምነትና የእውቀት አባቶችና ሊቃውንት ነው፡፡

ከላይ በወፍ በረር ያነሳሁትን የሀገራችንን ትውልድና መሪዎች ጠባይ ስናጤን ለጳጳሳት፣ ካህናት፣ ሸኾች፣ ዑስታዞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎ መሪዎች፣ የዘረኝነት ደቄ ያልለከፋችሁ የዩኒቭረሲቲ ፕሮፌሰሮች የባለጌ ልጆች ወላጅና አሳዳጊ የሆናቸሁት እናንተ ናችሁ ለማለት እደፍራለሁ፡፡

ልጆቻችሁ ከቤት ወጥተው ከባዕዳን ውለው ሀገራቸውንና ማንነታቸውን በወሬ ጠገብ ግልብ እውቀት ሲበክሉት እንደሚገባ አልሞገታችሁም፡፡ ይህ ስንፍና ነው፡፡ ይህ ስንፍና ልጆችንም ወላጆችንም የሚጠፋበት የእብደት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ዜጎች በቡድን በቋንቋ ተደራጅተው ሀገር ሊካፈሉ ድንበር የሰምራሉ፣ ጦር ያሠለጥናሉ፤ ወጣቶች ፈጠራና ሥራን ዘንግተው እንዴት አድርገው በአቋራጭ አንደሚከብሩ ያሰላሉ፣ የትኛው ቡድን የትኛውን ቢያጠቃ መሬት አንደሚሰፋው ያልማሉ፡፡

ነጠላ ድግሪ ከባዕድ ሀገር ተውሰው፣ ምላሳቸውን ስለው፣ ሕሊናቸውን ሸጠው ራሳቸውን መሪ ያደረጉ ዕድሜያቸው ከ50 ያልዘለሉ ካድሬዎችና አክቲቪስቶች ይህንን በሀሰት ትምህርት የተወናበደውን፣ በስሜታዊነት የነደደውን፣ በመንጋነት የታሰረውን ወጣት ወደ ጥልቅ ገደል እየነዱት ነው፡፡

ስለዚህ እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋና ደካማ ልጃችሁ ከፍተኛ ሥጋትና ጭንቀት ስለአደረብኝ የሚከተለውን ጥሪ በማኅበራዊ ሚዲያ እጮኻለሁና በምታምኑት አምላክ፣ ስለ ሕሊናችሁ፣ ስለ ልጆቻችሁ ብላችሁ በፍጥነት ይህን እብደት ከእብድ ገላጋዮች እጅ ወስዳችሁ ኢትዮጵያዊ (ሀገራዊ) መድኀኒት ስጡት፡፡

ያጣነው እውቀት፣ አደረጃጀት፣ ጥበብና ልምድ የለም፡፡ ከዚህ በታች የጠቃቀስነውን እንኳ ሀብት ወደ ተግባር ብንተረገመው ከዚህ ከቁልቁለት መንገድ ለመመለስ ያስችለናል፡-

1) ጳጳሳትና ካህናት በትምህርታቸውን በፍትሐ ነግሥታቸው
2) ሼኾችና ፁስታዞች – በሸሪአቸው
3) አባ ገዳዎች – በገዳ ሥርዓታችሁ
4) ጡልጣኑ – በመድዓ
5) ኮንሶ – በኾንሶ-ሤራ
6) አማሮው – በኢኼ ሥርዓት
7) ቡርጂው – በሙጭንታታ-ሤራ
8- የአምሓራውና የትግራዩ የጎበዝ አለቃና የአባት ሥርዓት
9) የዋጉ – ወይት-ኸሚርነይ
10) የራያው – አቦ-ገረብ ሥርዓት
11) የዋጅራቱ – የቃንጪ ወይንም የገረብ
12) ጉራጌው – በጆካ-ሤራ … ወዘተ

ከክርስትናና ከእስልምና፣ ከይሁዲነትና ከባህል እምነቶች፣ እንዲሁም ባህላቱን የመሠረቱ ፍልስፍናዎች ለኀገራችን በሽታ መታከሚያ መተኪያ የሌላቸው መድኀኒቶች ናቸውና ተሰባስባችሁ ይህን እብደት አክሙት፡፡

ወገኖቹን በሰፈር በቋንቋ ከፋፍሎ፣ በክልል ድንበር አሥሮ፣ በዘረኝነት ስብከትና በሀሰተኛ ታሪክ ትርክት አሳውሮ፣ በማይጨበጥ ግላዊ ታላቅ የመሆን ተስፎ አጨጭበርብሮ ግጭትን እያለማ፣ ሀገርን እያደማ የቆየው የጎሣ መሪ ሁሉ ማንነቱ የጠፋበት የነጠላ ድግሪ መቅሰፍት የመታው ድውይ ነውና ድረሱልን፡፡

የእናንነት እውቀት የኮርስ ውጤት አይደለም፣ ግኝቱ የአንደ ሊቅና ወይንም ፈላስፋ ሐቲት አይደለም፤ አሠራሩ ዘመን የወለደው ቀመር አይደለም፤ ይልቁኑ በብዚ ሺ ዘመናት ከባህል እና ከእምነት ብዝሀነት፣ ከስነ ምህዳር ውጥንቅጣዊ መስተጋብር በመውደቅና በመነሳት፣ በጦርነትና በሠላም፣ በጋብቻና በስደት፣ በገባርነትና አስገባሪነት፣ በጋብቻና በአምቻ፣ በጸሎትና በምክር ዘመናተርን የተሻገረ ሁለገብነት ያለው ነው፡፡ እንደ ዘመናዊው ከምን እንደተሠራ ሳናውቀው እንደምንውጠው የፈረንጅ ኪኒን አይደለም፡፡

ዛረዉኑ ተሰባሰቡ፣ የሚያምነው ገዝቱት፣ ከሀዲውን መንግሥት ያስተናግደው፡፡
ሰዎች ሲሞቱ ፍታትና ሰላት አድርጎ መቅበር ለነፍስ ይጠቅማል፤ በቁም ከእብደት መልሶ እንደ አራዊት ከመግደልና ለመገደል መመለስ ለንስሐ ያበቃል፡፡ ሁለቱም የእናነት ሥራዎች ናቸው፡፡

ፍቅር ጠፍቶና እብደት ነግሦ በዝምታ የምትመለከቱ ከሆነ ሃይማኖታችሁን የምትሰብኩት ከልባችሁ አምናችሁ ሳይሆን ምናልበት በተከታዮቻችሁ ላይ ለሚሰጣቸው መንፈሳዊ ሥልጣን በመጠቀም ሥጋዊ ፈቃዶቻችሁን ለማገልገል የምትተጉ አሳቾች ሊያሰኛችሁ ይችላል፡፡ ለነፍስም ለሥጋም የማትጠቅሙ ተብላችሁ ትውልዱ ዘመናዊ ድግሪ ያደነቆረውን ወጠጤ ተከትሎ ይጠፋላችኋል፣ እናንተም በልጆቻችሁ ደም ሕሊና የይወቅሳችኃል፣ ፈጣሪም ይጤቃችኋል፡፡

መንግሥት ባለሥልጣናት ሀገራዊ መድኀኒቶቻችንን በመናቅ፣ በፕሮፓጋንዳና በውጭ ገብ አማካሪ፣ በጊዜአዊ አሸነፊነት ፍላጎት ታውራችሁ የሀገር አባቶችን ወደጎን ከመግፋት በመቆጠብ እውነተኛ ድጋፍ ስጡ፡፡ ትህትና ይኑራችሁ፣ እውነተኛ ሁኑ፤ በገዛ እናታችሁ ላይ ጌም አትጫወቱ፡፡

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s