ፖለቲካ

“የእምነት ልብሳችንን ከምንቀይር የስጋ ሞታችንን እንመርጣለን”

“አልባሳታችን የምናወልቀው ስንሞት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ይህን አልባሳታችንን እንድንለውጥ መገደድ ማለት ለእኛ እምነታችንን እንድንሽር፣ በእግዚያብሔር ስም የተሰጠንን ክብር እንዲዋረድ ማድረግ ነው”

~”5ኛ ተከሳሽ የሆንኩት አባ ገ/ሥላሴ ወ/ሐይማኖት ወደዚህ ፍ/ቤት ለመምጣት የዕምነት ልብሴን እንዳወልቅ ስጠየቅ አላወልቅም በማለቴ ማዕረጋቸውንና የአባታቸውን ስም ያላወኳቸው ነገር ግን የደህንነትና ጥበቃ ኃላፊ መሆናቸው የሚታወቁ ገ/እግዚያብሔር የተባሉ የእስር ቤቱ ኃላፊ እያዩና እራሳቸው እያገዙ ተፈሪ የተባለ ወታደር የጎማ ዱላ በመያዝ ወደ አንድ ሰዋራ ቦታ ሊወስደኝ ሲሞክር መሰሶ ላይ ተጠምጥሜ እምቢ ብልም ልብሴን ከላየ ላይ ለመግፈፍ በኃይል እየጎተተ ያንገላታኝ ከመሆኑም በላይ አቅም አንሶኝ ከመሬት ወድቄ ከእነ ልብሴ መሬት ላይ ጎትቶኛል”

(የዋልድባ መነኮሳት ለፍርድ ቤት ካቀረቡት አቤቱታ የተወሰደ፣ ሙሉ ማመልከቻው ከስር ይገኛል)

የካቲት 13 ቀን 2010 ዓም

የኮ/መ/ ቁጥር 197866

ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት

አዲስ አበባ

ከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ

ተከሳሾች እነ ተሻገር ወልደሚካኤል

ጉዳዩ:_ በእስር ቤት አያያዝ ላይ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች እየደረሰብን ያለውን በደል ስለማመልከት ይመለከታል

አመልካቾች በዋልድባ ገዳም መነኮሳት ስንሆን ወንጀል ፈፅማችኋል በሚል ክስ ቀርቦብን በቂሊንጦ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ በእሰር ላይ እንደምንገኝ ይታወቃል።
አመልካቾች መነኮሳት እንደመሆናችን ሐይማኖታችን የሚያስገድደንን የራሳችን አልባሳት እንጠቀማለን። ይህን አልባሳታችን የምናወልቀው ስንሞት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ይህን አልባሳታችንን እንድንለውጥ መገደድ ማለት ለእኛ እምነታችንን እንድንሽር፣ በእግዚያብሔር ስም የተሰጠንን ክብር እንዲዋረድ ማድረግ እንደሆነ ይሰማናል። በመሆኑም የእምነት ልብሳችንን ከምንቀይር የስጋ ሞታችንን እንደምንመርጥ ለእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች በተደጋጋሚ ግልፅ አድርገናል። ይሁን እንጅ የእስር ቤቱ አስተዳደር መጀመርያ ላይ ተቃውሟችንን የተቀበለ የመሰለ በመሆኑ በእኛ በኩል ለዚህ ፍርድ ቤት አቅርበን የነበረውን አቤቱታ ሳንገፋበት ቀርተናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የእስር ቤቱ አስተዳደር አልባሳቱን እንድናወልቅ ከፍተኛ ጫና እያደረገብን ከመሆኑም በላይ ለከፍተኛ እንግልትና መዋረድ ተዳርገናል። ይኸውም :_

5ኛ ተከሳሽ የሆንኩት አባ ገ/ሥላሴ ወ/ሐይማኖት ወደዚህ ፍ/ቤት ለመምጣት የዕምነት ልብሴን እንዳወልቅ ስጠየቅ አላወልቅም በማለቴ ማዕረጋቸውንና የአባታቸውን ስም ያላወኳቸው ነገር ግን የደህንነትና ጥበቃ ኃላፊ መሆናቸው የሚታወቁ ገ/እግዚያብሔር የተባሉ የእስር ቤቱ ኃላፊ እያዩና እራሳቸው እያገዙ ተፈሪ የተባለ ወታደር የጎማ ዱላ በመያዝ ወደ አንድ ሰዋራ ቦታ ሊወስደኝ ሲሞክር መሰሶ ላይ ተጠምጥሜ እምቢ ብልም ልብሴን ከላየ ላይ ለመግፈፍ በኃይል እየጎተተ ያንገላታኝ ከመሆኑም በላይ አቅም አንሶኝ ከመሬት ወድቄ ከእነ ልብሴ መሬት ላይ ሲጎትተኝ በሌሎች ሀይ ባይነት የከፋ ጉዳት ሳይደርስብኝ ተርፌያለሁ። ያም ቢሆን በእምነቴ መፅናቴ እንደ ጥፋት ተቆጥሮብኝ ለአንድ ወር ያህል መቀጣጫ በሆነው ዞን 5 በከፋ ሁኔታ እንድቆይ ተደርጌያለሁ።

4ኛ ተከሳሽ የሆንኩት እኔ አባ ገ/እየሱስ በተመሳሳይ ችግር እየደረሰብኝ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ ሁለታችንም ተለዋጭ ልብስ እንዳይገባልን ተከልክለን በላያችን ላይ ያለው ልብስ በእጅጉ ቆሽሾ በጤናችን ላይ ችግር እያስከተለ ይገኛል። በሌላ በኩል 4ኛ ተከሳሽ በአሁኑ ጊዜ ፈፅሞ ባለወኩት ምክንያት እና ለምን ያህል ጊዜም እንደምቆይ ባለወኩበት ሁኔታ በቅጣት መልክ ዞን 5 እንድቆይ ተደርጌያለሁ። ይህ ቦታ ጥፋት ፈፅሟል የሚባል እስረኛ በቅጣት መልክ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ የሚደረግበት እጅግ አደገኛ እና ለከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የሚዳርግ መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ ነው።

በአጠቃላይ አመልካቾች በተከሰስንበት ጉዳይ ይህ ፍርድ ቤት ሊሰጥ የሚችለው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ አስቀድሞ በእስር ቤት እየደረሰብን ያለው በደል ግን እምነታችንን የሚያዋርድ እና ስብዕናችንን የሚነካ በመሆኑ ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ያቀረብነውን አቤቱታ ጭምር በማየት የአገሪቱ ሕገ መንግስት ለሀይማኖት ነፃነት የሰጠውን ጥበቃ መሰረት በማድረግ በደል የፈፀሙብን የእስር ቤቱ ሰራተኞችና ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድልን እንዲሁም በእስር ቤቱ አስተዳደር ላይም መብታችን የሚያስከብር ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እናመለክታለን

1ኛ) አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም

2ኛ) አባ ገ/ስላሴ ወ/ሐይማኖት

(መነኮሳቱ ነገ የካቲት 19 ቀጠሮ ያላቸው ሲሆን አቤቱታውም ለፍርድ ቤቱ ደርሷል)

በጌታቸው ሽፈራው

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s