ፖለቲካ

ቢመራችሁም ደግማችሁ ጠጡት፤ያሽራችኋል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ይድረስ
ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትና የሀገር መሪዎች በሙሉ፦

በቅድምያ እስከ ዛሬ ድረስ በግፍና መከራ ከእውነት በራቀ ምክንያት የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት በግዞት በጨለማ ስቃይ በየእስር ቤቱ ውስጥ አንገላታችሁ ልትዘልቁት አለመቻላችሁን ተገንዝባችሁና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት እንዳሸነፋችሁ አውቃችሁ፣ከፊታችሁም የተደነቀረውን የራሳችሁን የወደፊት የመከራ መንገዳችሁን አስባችሁ ከወዲሁ እየመረራችሁና ኢያቅለሸለሻችሁም ቢሆን ጥቂት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታታችሁ ሳላመሰግናችሁና ሳላደንቃችሁ አላልፍም።

ጥሩ ጅምር ነው በርቱ።ታዲያ የፖለቲካ እስረኞችን ብቻ ሳይሆን
የሃይማኖት መሪዎችን ፓትርያርኩን፣ሊቃነ ጳጳሳቱን፣በየእስር ቤቱ ያሉ መነኮሳቱን፣ቀሳውስቱን፣ዲያቆናቱን ወዘተ ከዚያ ሁሉ በበለጠ ደግሞ እራሳችሁንም እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር
ኃይለ ማርያም ተገፍታችሁ ሳይሆን ወዳችሁ በፈቃዳችሁ ፍቱ፣ፍቱ፣ፍቱ ወይንም ተፈታቱ።እናንተም እኮ ታስራችኋል።ምናልባት በሥልጣን ላይ ስላላችሁ በጠባቂዎቻችሁ ታጅባችሁ ዛሬ ስትታዩ ከእስር ነፃ የወጣችሁ መሰላችሁ? አይደለም፣አይምሰላችሁ።ታስራችኋል።ያልታሰረ በታጃቢ መች ይጓዛል?አንድ ገበሬ በክረምት ወራት የሚበላውን እህል ቢያጣ እርሻዬ ሲደርስ የምከፍልህ አንድ ቁና እህል አበድረኝ ኢያለ በብድር ሲበላ ከርሞ መኸሩን የሚሰበሰብበት ጊዜ ደርሶ ጤፉን አጭዶ ከምሮ ክምሩ ትልቅና ያማረ እንደ ሆነ ተመልክቶ ራሱን ኢየነቀነቀ “አይ አንቺ ክምር ያለሽ መስሎሻል፣በቁምሽ ተበልተሽ አልቀሻል”እንዳለው እናንተም በቁማችሁ ተበልታችኋል፣ታስራችኋልና ራሳችሁን ለመፍታትና ከሕዝቡ ጋር ለመቀላቀል ጣሩ።

ታዲያ ራሳችሁን ለመፍታት መጣር ዛሬ ልታደርጉ የምታስቡትና የምታውጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለም
መንገዱና መፍትሔው።እሱማ የበለጠ መታሰራችሁ ብቻ ሳይሆን መተብተባችሁ ነው።ከፊተኛው እስራችሁ የኋለኛው ትብትባችሁ እንዳይጎዳችሁ ተጠንቀቁ።ነገ ነገሮች ቢለወጡ ከጥቁት እስራታችሁ ሕዝቡ ሊፈታችሁ ምንም አይደለም ሊምራችሁና ሊፈታችሁ ይችላል።ነገር ግን እንደ ገና ወደ አሮጌው ጉዞ ወደ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንገድ ማቅናት ወደቀድሞ ትብትባችሁ መመለስ ከነትብትባችሁ ይተዋችኋል እንጂ አይፈታችሁም።

ምናልባት ወደ እዚህ ትብትብ ማለፋችሁ ነገሮች ቢመራችሁ፣ቢያቅለሸልሻችሁ፣የመሸነፍ ስሜት ቢሰማችሁ፣ሥልጣናችሁ ያበቃ ስለ መሰላችሁ፣ጊዜያችሁ ያለፈ መሆኑ ስለ ታያችሁ ወዘተ….. ይመስለኛል፣ነገሩ እውነት ነው። ግን ግድ የላችሁም ……ቢመራችሁም ደግማችሁ ጠጡት፤ያሽራችኋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብላችሁ ራሳችሁም በአስቸኳይ ነገር ከምትዋከቡና ከምትደናገሩ ማን ያውቃል? ይህ አስቸኳይ ነገር ሳታስቡት እናንተውኑ አዋክቦአችሁና አስቻኩሎአችሁ እንዳያጠፋችሁ ቀድማችሁ ሰላሙን መንገድ፣የሽግግር መንግሥቱን ነገር፣የብሔራዊ እርቁን ነገር፣የእናት ሀገርን ጉዳይ ማሰብ አይሻልም?ሀገር እኮ እናት ናት።

ልጅን ፈትቶ እናትን ማሰር ተገቢ ነው? ቀድማ ለልጆችዋ የታሰረች እናት ትፈታለች እንጂ።ለልጆችዋ እናታቸው መፈታት ነበረባት፣አለባትም።ታስረው የተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች የተባሉት ሁሉም እኮ ልጆችዋ ናቸው።የታሰሩትም ስለ እናት ሀገራቸው ስለ ኢትዮጵያ እንጂ ስለ ግል ጉዳያቸውና ሕይወታቸው አይደለም።በግል ሕይወታቸውማ ከማናቸውም የተሻለ ሕይወትና ኑሮ እንደ ማንኛውም ሰው ነበራቸው።

ስለዚህ የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሀገር መሪዎች ሆይ፦”አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ” እንደሚባለው የሀገራችን አባባል የነገው የእናንተም ሕይወት፣የቤተሰቦቻችሁ፣የዘመዶቻችሁ፣የወገኖቻችሁ ወዘተ…
ሕልውና በዚችው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ አብሮ
የሚመሰረት ነውና እባካችሁ አሁንም ደግሜና ደጋግሜ በቸሩ መድኃኔዓለም ስም የምላችሁ፣የምጠይቃችሁና የምማፀናችሁ
እስከ ዛሬ ከሰራችሁት በደላችሁ ሁሉ ዛሬ ልታደርሱት ኢየጣራችሁት ያለው በደላችሁና ጥፋታችሁ የበለጠና የከፋ ይሆናልና ይህም እንዳይሆን የጀመራችሁትን ታሪካዊ ሥራችሁን
እንደ ጀመራችሁት ስለ እራሳችሁ ጥቅም ሳይሆን ስለ ሀገር፣ስለ ሕዝብ ብላችሁ ሰላምን፣ፍቅርን፣መተሳሰብን፣እርቅን
ነፃነትን፣ፍትህን፣እኩልነትን፣አንድነትን፣ሀገርን፣ድንበርን፣ባንዲራን ወዘተ……ለሕዝቡ አስረክቡ።

ይህንን ለማድረግ መራራ ትግል ይጠይቃል፣መራራ ውሳኔን ይጠይቃል።የሕሊና ትግልና ውሳኔ ማለቴ ነው።ነገር ግን ብዙ ብዙ ሆድን የሚቆርጡ ተሐዋስያንን በሽታዎችን በሆድ ውስጥ ይዞ ከመንቆራጠጥና ከመንፈራገጥ ይህንን መራራውን የለውጥ የኮሶ መድኃኒት ጠጥቶ ዝንተ ዓለም መገላገል ይጠቅማልና “ቢመራችሁም ደግማችሁ ጠጡት፤ያሽራችኋል።”

በቅዱስ መጽሐፍ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፦
መዝ ፻፳፮፡ ፩፥፪
“እግዚአብሔር ቤትን ካልሰራ፥
ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤
እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥
ጠባቂዋች በከንቱ ይተጋሉ።
በማለዳ መገሥገሣችሁ ከንቱ ነው።” ይለናል።ስለ ቃሉ ስሙ
የተመሰገነ ይሁንና ይህንን ቅዱስ ቃል እናንተ መሪዎች
በማስተዋል ደግማችሁ ፀልዩት፣አንብቡት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” እንደ ተባለው ለብዙ ዘመናት ስለ መከራዋ፣ስለ ልጆችዋ ወደ ፈጣሪዋ አልቅሳለች።አሁን ፍርድና ጥበቃ ነው የምትጠባበቀው።ሕዝቧን የሚታደገው፣ቅጥሯን የሚሰራው፣
ቤቷን የሚጥብቀው እርሱ የሠራዊት ጌታ ቸሩ እግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለምና ከእግዚአብሔር ጋር ጠባችሁን አቁሙና ለእስከ ዛሬው ጥፋታችሁ በንስሐ ሕይወት ለመኖር ከእርሱ ጋር ተነጋገሩ፣ለይቅርታ ኑሩ።ቸሩ እግዚአብሔር ይህንን አሰስቦአችሁ እናንተንም፣ሕዝቡንም ሀገርራችንንም ከዳግም
ጥፋት ይታደጋት ዘንድ የእርሱ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን በማለት
በታላቅ አክብሮት አሳስባለሁ።

ቸሩ እግዚአብሔር
ሀገራችንን ኢትዮጵያንናሕዝቦችዋን በምሕረቱ ይባርክ!!!

ቀሲስ አሸናፊ ዱጋ ዋቄ
ከዋሽንግተን ዲሲ።
የካቲት ፲ ቀን ፪፼፲ ዓ.ም

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s