ዜና

Zemera Radio Weekly News 11,Feb,2018

 

ሰሞኑን ይፈታሉ የተባሉት የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ እያወዛገበ ነው

ሰሞኑን ይፈታሉ የተባሉት 746 የፖለቲካ እስረኞች መካከል የአንዳንዶቹ ጉዳይ እያወዛገበ ነው።የስርዓቱ ልሳን በሆኑ ሚዲያዎች የ18 ዓመት ፍርደኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የእድሜ ልክ ፍርደኛው አንዷለም አራጌና ሌሎች 746 እስረኞች እንዲለቀቁ መወሰኑን ቢገልፁም ከእስረኞች ጋር መግባባት አለመቻሉ ታውቋል።የሚለቀቁት የእስረኞች ዝርዝር በይቅርታ ቦርድ ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀርቦ ከጸደቀ በሗላ “የተሀድሶ” ስልጠና ወስደው እንደሚለቀቁ የፌዴራል አቃቤ ህግ ገልፆ ነበር።ይሁን እንጂ ከሚፈቱት እስረኞች መካከል ስማቸው በሚዲያ የተጠቀሰው ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣አንዷለም አራጌና አበበ ቀስቶ ከአንድም ሁለት ጊዜ “የአርበኞች ግንበት 7 አባል ነን ብላችሁ ፈርሙ” መባላቸውንና እነሱም “በሌለንበት ነገር አንፈርምም፤ያጠፋነው ነገር ስለሌለም ይቅርታ አንጠይቅም” ማለታቸው መገለጹ ይታወሳል።በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት “የይቅርታ መጠየቂያ ፎርም” ላይ እንዲፈርሙ ተጠይቀው አለመስማማታቸው ተገልጿል። ከ7-22 ዓመታት እስር ተፈርዶባቸው በእስር ቤት የሚገኙት አህመዲን ጀበል፣ ካሊድ ኢብራሒም፣ አህመድ ሙስጠፋና መሀመድ አባተ ሲሆኑ “ያጠፋነው ነገር የለም” በማለት ሳይፈርሙ መቅረታቸውን ከቤተሰቦቻቸው የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።ሰሞኑን ይፈታሉ ከተባሉት 746 የፖለቲካ እስረኞች መካከል በ2001ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ጄኔራሎች፣የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኑነት ሀላፊ ዮናታን ተስፋየ እንደሚገኙበት የተለያዩ መረጃዎች ጠቁመዋል። የአውራምባ ታይምስ ምክትል አዘጋጅ የነበረውና 14 ዓመት ተፈርዶበት በዝዋይ እስር ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ ከሚፈቱት መካከል ስሙ እንዳልተካተተም ለማወቅ ተችሏል።ስርዓቱ እነ እስክንድር ነጋን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ከእስር እንዲለቅ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች እየጠየቁ ይገኛሉ።

ለአስር ቀናት የተካሄደው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ተገለጸ። “እንደገና የመልማትና ፍሬ የማፍራት መንገድ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ ለአስር ቀናት የተካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ የተለያዩ ትኩረት የሚስቡ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ።ማዕከላዊ ኮሚቴው በኢህአዴግ ምክር ቤት ኦህዴድን ከሚወክሉ 45 አባላቱ 14ቱ በሌሎች አዳዲስ አባላት መተካቱን ገልጿል።ከተነሱት መካከልም ቀድሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የነበሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ ፣በሙስና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ዘላለም ጀማነህ የቀድሞው የኦሚያ ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሶፊያን አህመድ እንዲሁም የቀድሞው የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሀላፊ የነበሩት አቶ በከር ሻሌ እንደሚገኙበት ተገልጿል።ድርጅቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርም አብሮ ለመስራት ጥሪ አቅርቧል።
ማእከላዊ ኮሚቴው ለቀድሞው ፕሬዝደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቤት መኪና እንዳበረከተላቸው ታውቋል።ኦህዴድ ለዶ/ር ነጋሶ ካበረከተላቸው መኪና በተጨማሪም የህክምና ወጭና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች በፓርቲው እንዲሸፈንላቸው መወሰኑን አስታውቋል።ዶክተር ነጋሶ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በህግ የተደነገገላቸውን ጥቅማጥቅም እንዳያገኙ ተከልክለው መቆየታቸው ይታወሳል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው በሀገሪቱ የንግድ ስርዓት ከአድሎ ነፃና ሁሉንም ህብረተሰብ እኩል ያሳተፈ እንዲሆን እንደሚሰራና የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲቀጭጭ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት በህግ እንደሚጠይቅ ገልጿል። የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ነጻነቱን ጠብቅ እንዲሰራ የክልሉ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል።ባለፈው ወር የህወሓቱ ብሮድካስት ባለስልጣን ዘርዓይ አሰግዶም የኦሮሚያ ብሮድካስቲግ ኔትወርክና የአማራ ቴሌቪዥን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ግጭት በማባባስ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው የሚዲያ ተቋማት መካከል ነበሩ በማለት መፈረጁ የሚታወስ ነው።

ከሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ እንደሚካሄድ ተገለጸ

ከነገ ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ አድማው በሚደረግባቸው ቀናት ውስጥ ምንም ዓይነት የስራ እንቅስቃሴ እንደማይካሄድ ተገልጿል፡፡ በቄሮዎች እንደተጠራ የተነገረለት የሦስት ቀናቱ ህዝባዊ የስራ ማቆም አድማ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ የቀረበ ሲሆን በህወሓት አገዛዝ የተገሸገሸ ሁሉ በስራ ማቆም አድማው እንዲካፈል ተጠይቋል።አድማው በሚተገበርባቸው ከተሞች ምንም አይነት የትራንስፖርትም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ስለማይኖር ህብረተሰቡ ለሦስት ቀናት የሚሆን የምግብም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ሸቀጦችን እንዲያሰናዳ አዘጋጆቹ አሳስበዋል። የስራ ማቆም አድማው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የህዝባዊ ተቃውሞው አንድ አካል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ማካሄድ ያስፈለገውም የህወሓትን አገዛዝ ለማስጨነቅና ስልጣን እንዲለቅ ለማስገደድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡በቅርቡ ስራ የጀመረው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርም አገልግሎት እንዳይሰጥ ቄሮዎች(ወጣቶች) አስጠቅቀዋል።ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተለያየ ጊዜ የተሳካ ህዝባዊ የስራ ማቆም አድማ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ” አዳዲስ የስራ ሀላፊዎችን ሹመት አጸደቀ

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢና ሰባት የቦርድ አባላትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ማፀደቃቸው ተገለጸ። በዚህ መሰረትም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በመሆን መሾማቸው ታውቋል።አምባሳደር ሳሚያ ከ1998 እስከ 2009ዓ.ም በማዕከላዊ ስታስትቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር ሆነው ለረጅም ዓመታት የሰሩ ሲሆን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በናይጀሪያ አምባሳደር ሆነው እየሰሩ እንደነበረም ተጠቅሷል። የኦሮሚያ ክልል የህገ መንግስት ትርጉም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ ነበሩ የተባሉት አቶ ደሞዜ ማሜ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው ታውቋል።የቦርድ አባላት በመሆን ወ/ሮ የሺሃረግ ዳምጤ፣ ፕሮፌሰር ፋንቴ አባይ፣ ወ/ሮ ፀሀይ መንክር፣ አቶ ተካልኝ ገብረሥላሴ፣ አቶ ጀማል መሐመድና አቶ ሀብቴ ፍቻላ መሆናቸው ተገልጿል።
አምሳደር ሳሚያ ዘካሪያ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን በዋና ዳሬክተርነት በመሩበት ወቅት “የአማራ ህዝብ” በ2.4 ሚሊዮን ቀንሶ በመገኘቱ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበረ የሚታወስ ነው።የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓት አንድ ቅርጫፍ መስሪያ ቤት እንደሆነና በነፃ ምርጫ ስም የስርዓቱን እድሜ ማራዘሚያ ተቋም ነው በሚል በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ አመኔታ እንደሌለው ይታወቃል።

የአጼ ቴዎድሮስ ሐውልት በደብረታቦር ከተማ ተመረቀ

የአፄ ቴዎድሮስ የመታሰቢያ ሐውልት በደብረ ታቦር ከተማ ዕሮቡ እለት ተመረቀ።በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የገነባው የመታሰቢያ ሐውልት 7.5 ሜትር ርዝመት ሲኖረው ሁለት ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት ተገልጿል።ሐውልቱ ከአፄ ቴዎድሮስ በተጨማሪም ለልጃቸው ለልዑል አለማየሁና ለጦር መሪያቸው ለፊታውራሪ ገብርየም ጭምር እንቆመ ታውቋል።አፄ ቴዎድሮስ ከ1847 እስከ 1860ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሰ-ነገስት በመሆን ለ13 ዓመታት ኢትዮጵያን “አንድና ዘመናዊ” ሀገር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ጠንካራ መሪ እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ይዘክራል።

ወደ ባህር ተገፍትረዋል የተባሉ 25 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የደረሱበት አንዳልታወቀ አይ. ኦ. ኤም አስታወቀ

የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) ትናንት ማምሻውን እንዳስታወቀው 25 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ባህር ተገፍትረው ከተጣሉ በሗላ የደረሱበት እንዳልታወቀ ገለጸ።በየመን በአራት ጀልባዎች ሲጓዙ ከነበሩ 600 በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መካከል 25 የሚሆኑት ወደ ባህር ተገፍትረው እንደተጣሉ የአይ.ኦ.ኤም (IOM) ቃል አቀባይ ጆኤል ሚልማን ተናግረዋል።ቃል አቀባዩ እንደገለጹት ወደ ብህር ተገፍትረው የተጣሉት 25 ኢትዮጵያዊያን በህይወት ይኖራሉ ብለው እንደማያምኑም ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 87 ሺህ ስደተኞች ከጅቡቲ በመነሳት የእርስ በእርስ ጦርነት ቀጠና በሆነውና 8 ሚሊዮን ህዝቧ የተራበባትን የመንን እንደ መሸጋገሪያነት እንደተጠቀሙ የአይ.ኦ.ኤም ቃል አቀባይ ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊያን ጨምሮ ከአፍሪካ የሚነሱ በርካታ ስደተኞች ሜዲትራሊያን ባህር በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ በአሸጋጋሪዎቻቸው ወደ ባህር እየተገፈተሩ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ሲዘገብ ቆይቷል።

የ2018ቱ የክረምት ኦሎምፒክ በደቡብ ኮሪያ ፒዮንግቻንግ እየተካሄደ ነው

የ2018ቱ የክረምት ኦሎምፒክ በደቡብ ኮሪያዋ ፒዮንግቻንግ ከተማ አርብ እለት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው።በዚህ በውድድር ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊ ሲሆኑ ናይጄሪያ፣ ኤርትራ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ቶጎ ተወካዮቻቸውን ወደ ደቡብ ኮሪያ መላካቸው ታውቋል።የዘንድሮው የክረምት ኦሎምፒክ ትኩረት ከሳቡት መካከል በሁለቱ ኮሪያዎች ያለው የፖለቲካ ባላንጣነት በአጻራዊነትም ቢሆን ወደ ተሻለ ደረጃ የተሻገረበት በመሆኑ ነው።የሰሜን ኮሪያ የስፖርት ቡድን በሀገራቸው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት በኪም ዮን ጆንግ የተመራ ሲሆን ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኡን ጋርም ትናንት ቅዳሜ መገናኘታቸው ተዘግቧል።የሰሜን ኮሪያው መሪ ለደቡብ ኮሪያው አቻቸው በተመቻቸው ጊዜ ፒዮንግያንግን እንዲጎበኙ ግብዣ ቀርቦላቸዋል።ሰሜን ኮሪያ እየገነባች ባለችው የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ምክንያት በተባበሩት መንግስታትና በአሜሪካ የተለያዩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀብ እንደተጣለባት የሚታወስ ነው።

 

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s