ፖለቲካ

ታቦቱ ፊት መገደል መቼ ነው የሚያበቃው? (በቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

ታቦት በቆመበት ሰውን መግደል አዲስ የዘመኑ አሰቃቂ ወንጀል ነው። በቅ/እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ባህታዊ (ባህታዊ ፈቃደ ሥላሴ?) ሕዝቡም ፓትርያርኩም በተሰበሰቡበት ከተገደሉ ወዲህ ታቦት አቁመን ሰው መግደልን፣ ለታቦት የሚገባውን ክብር መንፈግን እየተለማመድነው ነው። ከ1997 ዓ.ምሕረቱ ምርጫ ቀጥሎ በመጣው የጥምቀት በዓል ላይ አስለቃሽ ጢስ በመተኮስ ታቦቱን የያዙ ካህናት ላይ ሳይቀር ምን ያህል ወንጀል እንደተፈፀም እናስታውሳለን።

አሁን ይባስ ተብሎ በዓላቸውን ለማክበር የወጡ የወልዲያ ወጣቶች ላይ በጅምላ ተኩስ ብዙ ግድያ መፈፀሙ ይኸው እየታየ ነው። ከቅ/ሚካኤል ዕለት የጀመረው ግርግር አሁንም እንዳልቆመ እየሰማን ነው። የወልድያ ወጣቶች በምን ዓይነት ጥይት ተገደሉ? በክላሽ ወይስ መኪና ላይ በተጠመደ ከባድ መሣሪያ እና ከሕንጻዎች አናት ላይ በሚተኮስ የአልሞ ተኳሾች አረር የሚለውን አንስቼ ጉንጭ አልፋ ክርክር ማድረግ አልፈልግም። ይሁን እንጂ የወልዲያውን ግርግር የሚያሳይ ቪዲዮ ላይ የሚሰማው የጥይት ድምጽ የክላሽና የሽጉጥ ድምጽ እንዳልሆነ ግን ለመገመት ብዙም አይከብድም። ጥይት ሲተኮስ ሰምቶ የሚያውቅ ማንም ሰው ሊለየው የሚችለው ነገር ነው። (ዝረዝሩን ለሙያው ባለቤቶች ልተወው)

መጀመሪያውኑስ እንዲህ የታጠቀ እና ከባድ መሣሪያ ያለው «ጦር» መሐል አገር ምን ያደርጋል? አንደኛውኑ ሕዝቡ በጠላትነት ካልተፈረጀ በስተቀር። እነ እንቶኔ ሱቃችን ተቃጠለ የሚሉት ልቅሶ ሌላ ቂም በሰው ልቡና እንዲቋጠር ከማድረግ ያለፈ ምንም ትርጉም ያዘለ ሐሳብ ስላልሆነ ለውይይት እንኳን ላነሳው አልፈቅድም። ደግሞስ ድንጋይ ለወረወረብህና ለሰደበህ ሁሉ ጥይት በማጉረስ አገር ማስተዳደር የሚባል ፈሊጥ ከየት የመጣ ነው። በርግጠኝነት ይህ «ለድንጋይ ውርወራ ጥይት» መለወጥ የሚባል ነገር ያለው ሕዝቡ ሕዝብህ ካልሆነ ብቻ ነው።

ለዚህ ነው የዚህ ወንጀለኛ ፓርቲ አገዛዝ «አምባገነንነት» ሳይሆን «ቅኝ ገዢነት» ነው የምንለው። ልድገመው። አገሪቱን እያስተዳደራችሁ ያላችሁት እንደ ቅኝ ገዢ ኃይል ነው። አምባገነንነትን በዘመነ ደርግ እናውቀዋለን። በጅምላ መታሰርንና መገደልንም ቢሆን በዘመነ ደርግ እናውቀዋለን። አገራችን በደርግ የደረሰባት ቁስል መልኳን አስቀያሚ አድርጎታል። ነገር ግን እስከዚያ አስቀያሚነቷ መኖር ችላ ነበር። የዚህ ዘመኑ በሽታ ግን ቆዳን የሚቀይር የላይላይ በሽታ ሳይሆን ካንሰር ነው። ካንሰር ደግሞ ለጊዜም መቆጣጠር ይቻል ካልሆነ ዞሮዞሮ መግደሉ አይቀርም። አገራችንን የተጣባት ካንሰር ነው፡፡ ጥያቄው ካንሰሩ ተስፋፍቷል ወይስ በሰውነት ሙሉ አልተሰራጨም የሚለው ነው። ሥጋታችን መላውን ሰውነት ከሚያበላሽበትና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከሚገድልበት ደረጃ የደረሰ መስሎን ሁላችንም አዝነን ነበር። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት እንዳልጠፉ፣ በወንዝና በቋንቋ ልዩነት እንዳልመከኑ ግን ዓይተን ደስታችንን አጣጥመን ሳንጨርስ ይህ ደስታ የማይመቸው አካል በውኃ ሊጠመቅ የወጣውን ምእመን በደም አጥምቆ ደስታችንን አደብዝዞታል።

በግፍ የተጨፈጨፉትን በሙሉ ነፍሳቸውን ይማርልን። መታወቅ ያለበት ነገር ግን ይህንን ግፍ መቸም አንረሳውም። ይቅር ብንላችሁም ግን አንረሳውም። ደግ ዘመን ሲመጣ ወልዲያም እነዚህን ልጆቿን የምትዘክርበት እና እንዲህ ያለው ግፍ እንዳይደገም ለስማቸው ምልክት የምታቆምበት ቀን ይመጣል። በታቦታችን ፊት መገደላችን የሚያበቃበት ዘመን ይመጣል። ይዘገያል እንጂ አይቀርም።

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s