ዜና

Zemera Radio Weekly News 03 Dec,2017

የተከበራችሁ አድማጮቻችን ከዘመራ ራዲዮ የአክብሮት ሰላምታችን ይድረሳችሁ ሳምንታዊ ዝግጅቶቻንን ይዘን ቀርበናል በመግቢያው ላይ እንዳደመጣችሁት እራሴን ገምግሚያለሁ ያለው ሕወሓት ሹም ሽር እንዳደረግ አስታውቋል ይህን በዝርዝር እንመለከተዋለን የሚዲያ ዳሰሳም አድርገናል አብራችሁን ትቆዪ ዘንድ በአክብሮት እንጋብዛለን አዝጋጅተን የምናቀርብላችሁ አርሴማ መድህኑ እና ቶማስ ሰብስቤ በጋራ በመሆን ነው መልካም ቆይታ

ህወሓት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ሊቀ መንበሩ አድርጎ መረጠ
ላለፈው አንድ ወር ዝግ ስብሰባውን ሲያደርግ የከረመው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን ሊቀ መንበሩ አድርጎ መምረጡን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ቀጣዩ የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረጽዮን ሲሆኑ ምክትላቸውም በቅጽል ስማቸው ሞንጆሪኖ እየተባሉ የሚጠሩት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ለአንድ ወር ያህል በዝግ የተካሄደው የህወሓት ስብሰባ ላይ የእነ አቶ ስብሓት ነጋ ቡድን የበላይነት እንደያዘ ውስጥ አዋቂዎች የገለጹ ሲሆን ለረጅም ጊዜ የፓርቲው ቁንጮ ሆኖ የቆየውን አባይ ወልዱን እንስቶ ዶክተር ደብረጽዮንን የድርጅቱ ሊቀ መንበር አድርጎ ለመሾም እንዳስቻለው ተገልጿል።ህወሓት ከሊቀ መንበሩ በተጨማሪ የተጓደሉ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትንም መምረጡን አስታውቋል፡፡ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ዶክተር አዲስአለም ባሌማ፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ አለም ገብረ ዋህድ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አቶ ጌታቸው አሰፋና ዶክተር አብርሃም ተከስተን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባላት አድርጎ መርጧል፡፡ ፓርቲው ስብሰባውን እንዳጠናቀቀ ቢገልጽም አሁንም ያልተፈቱ በርካታ የውስጥ ችግሮች መኖራቸውን የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።በቅጽል ስማቸው የሙስና እናት እየተባሉ የሚጠሩት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ላይ እግድ የተጣለ ሲሆን የተጣለው ዕግድ ላይም የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ታውቋል።ህወሓት እራሴን ገምግሜ በሙሉ ቁመናየ ተመልሻለሁ ቢልም ሹም ሽሩም ሆነ እግዱ አንድ ሥርወ መንግስት ገርስሶ ሌላ ሥርወ መንግስት ስልጣን እንዲይዝ ያደረገ የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ነው የሚሉ አስተያየቶች በርክተው ሰንብተዋል።ቶማስ ሰብስቤ የሰሞኑ የሕወሓት ሹም ሽር ያስተናገደውን ትችት ይዞላችሁ ቀርቧል

ኢትዮጵያ 27 የስደተኛ ካምፖችን ለመዝጋት መወሰኗን አስታወቀች
የኢትዮጵያ መንግስት 27 የስደተኛ መጠለያ ካምፖችን በአስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመዝጋት ማቀዱንና ስደተኞችንም ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታወቀ።ከደቡብ ሱዳን፣ኤርትራ፣ሶማሊያና ከየመን የመጡ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኛች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖሩ ተገልጿል።ካምፑን በመዝጋት ስተደተኞቹን በግብርና፣በንግድና በሌሎች የስራ ዘርፎች ለማሰማራት ማቀዱን የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት አስታውቋል።በጠመንጃ ሀይል እድሜውን እያራዘመ ያለው የኢትዮጵያ የአገዛዝ ቡድን በቅርቡ እንኳን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ እንዲሁም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ከስደት የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ባሉበት ሀገር ይህን ማቀዱ ከምዕራባዊያን መንግስታት የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት የታለመ ነው የሚል ትችትም እየቀረበበት ይገኛል።ከዚህ በፊትም በስደተኞችና በጸረ-ሽብር ዘመቻ ሰበብ ከምዕራባዊያን መንግስታት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድጋፍ ሲያገኝ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።

ሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያዊያንን በግዳጅ እያስወጣች ነው ተባለ
የሳዑዲ አረብያ መንግሥት ያለ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎችን በግዳጅ ወደየ ሀገራቸው መመለስ መጀመሩ ን ገለጸ። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሐሙስ እለት እንዳስታወቀው ሳውዲ አረቢያ ባለፉት ትንሽ ቀናት ብቻ ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ በላይ ኢትዮጵያዊያንን በግዳጅ ወደ ሀገር ቤት እንደመለሰች አስታውቋል።ሳወዲ አረቢያም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሀገሯ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎችን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አስወጥታ እንደምትጨርስም መግለጿን የሀገሪቱ የሚዲያ ተቋማት ዘግበዋል። ሙሉጌታ ተሾመ ለ17 ዓመታት በሳውዲ አረቢያ እንደኖረ ገልጾ “ከዚህ በፊትም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች በሀይል የማስወጣት ልምድ ሳውዲ አረቢያ ቢኖራትም እንደ ዘንድሮ አይነት እጅግ የከፋ እርምጃ ግን አይቶ እንደማያውቅ ለዜና ክፍላችን አስተያየቱን ገልጿል። ቀንና ሌሊት ፍተሻው ተጠናክሮ መቀጠሉንና ህጋዊ የመኖርያ ፈቃድ ይዘውም ከእግልት እንዳላዳናቸው በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገልጸዋል።የሳውዲ መንግሥት በሀገሪቱ ህጋዊ የመኖርያ ፈቃድ የሌላቸዉ የዉጭ ዜጎች በ90 ቀናት ዉስጥ ወደየሀገራቸዉ እንዲመለሱ የሚደነግግ የምህረት አዋጅ ባለፈው መጋቢት ወር ካወጣ በሗላ፤ አዋጁን ከሁለት ጊዜ በላይ ተራዝሞ ተጠናቋል።የምህረት አዋጁን ተከትሎ 70 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው የተገለጸ ቢሆንም አሁንም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ያለ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ በሳውዲ እንደሚገኙ ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው መስከረም ወር መግለጹ ይታወቃል።

የአቶ ዮናታን ተስፋዬ የሽብር ክስ ወደ መደበኛ ወንጀል ክስ ተቀየረ
የጸረ-ሽብርተኝነት ህጉ አንቀጽ 6 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ሽብርን በማበረታታት ወንጀል ተፈርዶበት የነበረው ዮናታን ተስፋዪ የ ሶስት አመት እስር ተቀነሰለት። የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ የተመሰረተበት የሽብር ክስ ወደ መደበኛ ወንጀል ክስ ተቀይሯል፡፡ ባሳላፍነው ሳምንት በፊደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አቶ ዮናታን ተስፋዪ ጥቅምት 24 2010ዓ/ም የፊደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ አንደኛ ወንጀል ችሎት የይግባኝ አቤቱታ ክርክሩን ማሰማቱ ይታወሳል። ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ህዳር 18/2010 ዓ/ም የአክቲቪስት ዮናታን ተስፋዪን የእስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅሬታ ነጥቦች እንደመረመረ በመገለጽ ይግባኝ ባዪ በእስር ፍርድ ቤት በቀረበበት የአቃቤ ህግ ማስረጃ ሰለመሆኑ የሚያሳይ ማሰረጃ አለመቅረቡን እንዳረጋገጠ በመገለጽ ከሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ነጻ ነው ብሎታል።በዚህም ምክንያት በመደበኛ ወንጀል ችሎት ሶስት አመት ከስደስት ወር እንደተፈረደበት ታውቋል። አቶ ዮናታን ተስፋየ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ በጻፋቸው ጽሁፎች የተነሳ በሽብር ወንጀል ተከሶ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር ተፈርዶበት እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ወደ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ክሱም በወንጀል ህጉ 257/ሀ እንዲሆን መወሰኑ ታውቋል፡፡ዮናታን ተስፋየ ከታህሳስ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በግፍ ታስሮ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የውጪ ዜና
ኬንያ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ መፍቀዷን ገለጸች
የኬንያ ፕሬዚዳንት ሁሩ ኬንያታ ባለፈው ማክሰኞ የሁለተኛ ዙር የፕሬዚዳንትነት ቃለ መሀላ ሲፈጽኑ ባደረጉት ንግግር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ያለምንም ቪዛ ሀገራቸውን መጎብኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።ኬንያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችውም የፓን አፍሪካንዝም ትልም እውን እንዲሆን ያላትን ቁርጠኝነት ለማሳየት እንደሆነ ፕሬዚዳንት በባዓለ-ሲመታቸው ወቅት ይፋ አድርገዋል። የምሥራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ዜጎችም በመታወቂያ ካርድ ብቻ በኬንያ መኖርና መስራት እንደሚችሉ ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልጸዋል። በባዓለ- ሲመቱ ላይ የ20 ሀገራት መሪዎችና 40 በላይ የውጭ ዲፕሎማቶች መታደማቸውንም ተገልሷል።ባለፈው ነሐሴ ወር የተካሄደውን የኬንያ ምርጫ በፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በሗላ በድጋሜ ጥቅምት 26 የተካሄደው ፕሬዚዳንሺያል ምርጭ በፍርድ ቤት ተቀባይነት በማግኘቱ ሁሩ ኬንያታ ለሁለተኛ ዙር የኬንያ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።የሀገሪቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ምርጫውን ቦይኮት ማድረግ ያልተሳተፉ ሲሆን በነሐሴ ወር ያሸነፍኩት እኔ ነኝ በማለት በሚቀጥለው ታህሳስ 12 ቃለ መሀላ እንደሚያደርጉ አስተውቀዋል።ይህም ሀገሪቱ ላይ ውጥረት መንገሱን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ውድ አድማጮቻችን ለዛሬ ያልናቸው ዜናዎች እነዚህ ነበሩ ከቀሪ ዝግጅቶቻችን ጋር መልካም ቆይታ

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s