ዜና

Zemera adio Weekly News 19,Nov,2017

ሰላም ጤና ይስጥልኝ የተከበራችሁ አድማጮቻችን የዘመራ ራዲዮ ሳምንታዊ ዜና ስለምታዳምጡን እናመስግናለን

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ለሶስት አመት የሚያገልግሉትን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ኦስሎ ከተማ ውስጥ አደረገ።

የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት የመከረበት ሰነድ ይፋ ሆነ

በህወሓት ውስጥ እርስ በእርስ የመጠቃቃት እና የዝምድና አሰራር መኖሩን  አርብ እለት ባወጣው መግለጫ ገለጸ

 

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ለሶስት አመት የሚያገለግሉትን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ በኦስሎ ከተማ አካሂዷል።

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ትናንት ቅዳሜ ህዳር 9፣2010 ዓም በኦስሎ ከተማ  ባደረገው የአባላት ስብሰባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱን መርጧል። የማኅበረሰቡ አማካሪ ቦርድ አባላት በአቶ የሱፍ፣ በዶ/ር ሙሉዓለም እና በዶ/ር ሰይፉ አስመራጭነት አምስት የስራ አስፈፃሚ አባላት ተመርጠዋል።በእዚህም መሰረት 1/ አቶ ፍቅሩ 2/ ወጣት ስርጉት፣ 3/ወጣት ማርታ 4/ አቶ አያሌው እና 5/ አቶ ለገሰ  ሲሆኑ በሰብሳቢነት አቶ ፍቅሩ ተመርጧል።በእዚህ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ለበርካታ ዓመታት በኖርዌይ የኖሩ ኢትዮጵያውያን በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በረጅም ጊዜ የስራ ዘመኑ ሙሉ በሙሉ በወጣት የሰው ኃይል በመተካቱ  መደሰታቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጠዋል።የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ እንቅስቃሴ የጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1987 ዓም እንደሆነ የማኅበረሰቡ ድረ ገፅ ያስረዳል።የአዲሱ ትውልድ ወደ አመራር መምጣት በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጋራ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያንፀባርቁበት የጋራ መድረካቸው እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። ምርጫው ከመደረጉ በፊት የአማካሪ ቦርዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት የኢ-ሜል መረብ አማካይነት ከሁለት ወራት በፊት ቅስቀሳ ሲያደርግ ነበር። በዛሬው የምርጫ ሂደት የተደሰቱት በኖርዌይ ለረጅም ዓመታት እንደኖሩ የሚነገረው አቶ ካሳ በኢትዮጵያውያን የኢ-ሜል መረብ ዛሬ ማምሻውን በላኩት የደስታ መልዕክት እንዲህ ብለዋል: –

“የተሰራው ስራ በጣም የሚመሰገን  ነው  በቦርድ ኮሚቲዎች በተደረገው ዝግጅት ለመልካም ውጤት በቃን ዛሬ። እስካሁን አይቸው የማላወቀው ለውጥ ነው ያየሁት አጠር መጠን ያለ ስብሰባ ነበር። እንደዚህ አይነት ደስ የሚል ስብሰባ የመጀመርያዪ  ነው ”  ብለዋል።እንዲሁም የተለያዪ ግለሰቦች አስተያየት የሰጡ መሆኑን ጉዳያችን የተባለው ድህረ ገፅ በስፋት ዘግቧል

የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት የመከረበት ሰነድ ይፋ ሆነ

እራሱን “የብሄራዊ ደህንነት” ም/ቤት ብሎ የሚጠራው ተቋም አርብ እለት የመከረበት ሰነድ ይፋ ሆኗል። የጨቋኙን ስርዓተ-መንግስት እድሜ ለማራዘም ደፋ ቀና እያለ የሚገኘው “የደህንነት” መስሪያ ቤቱ ባለፈው አርብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የክልል አስተዳዳሪዎች፣ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ሀላፊዎች የተካተቱበት የሀገሪቱን “ወቅታዊ ሁኔታ” በተመለከተ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወይይት መደረጉን አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ውይይት የተደረገበትና ለሚቀጥለው አንድ ዓመት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለ ሰነድ ማክሰኞ እለት በአዲስ ስታንዳር በኩል ይፋ ተደርጓል። ሰነዱ 26 ገፆች ያሉት ሲሆን “ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ ትንታኔ መሰረት ያደረገ የጸጥታ እቅድ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። “የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት አደጋዎች በአግባቡ በመተንተንና የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት በመንግስት የተነደፈውን ሀገራዊ እቅድ እንዲሳካ፤ እየታዩ ያሉትን ከፍተኛ የማስፈጸም ድክመቶችና የጸጥታ ችግሮች ማስተካከል እንደሚገባ” በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።በሰብዓዊ  መብት ጥሰቶች ምክንያት የውጭ እርዳታ በእጅጉ መቀነሱ፣ቀድሞ ከነበረው የኢንቨስትመንትና የቱሪስት ፍሰቱ  በጸጥታ ምክንያት በመዳከሙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዳደቀቀው በሰነዱ ተብራርቷል።የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ያለውን የፍትህ፣ የነፃነትና የእኩልነት ትግልን የግብጽና የኤርትራ መንግስታት በማቀናበርና ድጋፍ በማድረግ ከጀርባው እንዳሉ ተገልጿል። ሰነዱ በርካታ ግቦች  እንዳሉት የተዘረዘረ ሲሆን “ህግ-ወጥ” የሚሉትን ሰልፍ በሀይል ማስቆም የሚለው ተሰምሮበታል።

በህወሓት ውስጥ እርስ በእርስ የመጠቃቃት እና የዝምድና አሰራር መኖሩን  አርብ እለት ባወጣው መግለጫ ገለጸ

 በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ውስጥ እርስ በእርስ የመጠቃቃት ባህልና የዝምድና አሰራር በፓርቲው ውስጥ መንገሱን ፓርቲው አርብ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ባለፈው መስከረም ወር ተጀምሮ ያልተጠናቀቀው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት መፈጠሩ ሲዘገብ ቆይቷል።የህወሓት አመራሮች መግባባት ስለተሳናቸው ስብሰባው  ለአንድ ተጨማሪ ሳምንት የተራዘመ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት ለመቋጨት ዕድቅ መያዙም ታውቋል፡፡ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዳለው ከሆነ፣ አሁን ያለውን የፓርቲ አመራር በቀጣይ በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ለውጥ ለማድረግ ዕድቅ መያዙን ገልጿል፡፡ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት  የእነ ስብሰሓት ነጋ ቡድን  የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑትን አቶ አባይ ወልዱን ከህወሓት ሊቀ መንበርነት አንስቶ  በዶ/ር ደብረጽዮን  የመተካት ፍላጎት እንደነበረው ሲገለጥ ቆይቷል።ባለፈው ሳምንት በመቀሌ ከተማ ሲካሔድ በነበረው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ሌላ አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውን የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ፓርቲው በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ትርምስ ላይ ሲሆን፣ አመራሮቹም እርስ በእርስ መግባባት እንደተሳናቸው ታውቋል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን ወደማጠናቀቁ ተቃርቧል ቢባልም፣ በአንዳንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ መግባባት እንዳልተቻለም ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በመቱ  ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ገለጹ

በመቱ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ለወራት በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ለመውጣት እንደተገደዱ ከትናንት በስቲያ አርብ እለት ገለጹ። በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ወስጥ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩንና በዩኒቨርሲቲው የአስተዳድር አካላት በኩል በደል እየደረሰብን ነው በማለት ከአርብ ጀምረው ግቢውን ለቀው መውጣት መጀመራቸውን ከተማሪዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የሀገር ሽማግሌዎች፣የኦሮሚያና የአማራ ክልል ባለስጣናት፣ የፌዴራል መንግስቱ አካላትና ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር አርብ ውይይት ቢደረግም የተማሪዎች ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ያለ ስምምነት ተጠናቋል። እንደ ተማሪዎቹ ገለጻም ከማንም ጋር የብሄር ግጭት እንደሌለባቸውና ከኦሮሞ ተማሪዎች ጋርም መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።ተማሪዎቹ ትናንት ቅዳሜ ከአባ ገዳዎች፣ከሀይማኖት አባቶችና ከኦሮሞ ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ምክክር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለመቆየት መስማማታቸውንና የተወሰኑ ተማሪዎችም እንደተመለሱ ትናንት ባገኘነው መረጃ ለማወቅ ችለናል።

መቱ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን በከፍተኛ የጸጥታ ችግር የጀመረ ሲሆን እስካሁን መደበኛውን የመማር ማስተማር ሂደት አለመጀመሩም ታውቋል።ከዚህ ቀደምም የትግራይና የሶማሌ ክልል ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።ከ120 በላይ የሚሆኑ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች ወደ ጋምቤላ ክልል በማምራት በፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደሚገኙ  የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

 በሻሸመኔ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ተኩሰው ገድለዋል የተባሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በእድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ጥቅምት ወር አምስት ሰላማዊ ሰልፈኞችን ተኩሰው የገደሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን   በእድሜ ልክ እስራት ቀጣ። በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ ባለፈው ጥቅምት ወር አምስት ሰላማዊ ሰልፈኞችን ተኩሰው የገደሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እያንዳንዳቸው  የእድሜ ልክ እስራት ተላልፎባቸዋል።አብርሀም ጌታነህ፣አብርሀ ተክላይና ዘርፋ ሰንበቶ የተባሉ  የፌዴራል ፖሊስ አባል የነበሩ ሶስቱ ግለሰቦች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን እየገለጹ የነበሩ አምስት ንጹሀን ዜጎችን ተኩሰው መግደላቸው ተረጋግጦ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በሺህ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞችን የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በጸራራ ጸሀይ ተኩሰው ቢገሉም እስካሁን ማንም ተጠያቂ የተደረገ አካል አለመኖሩ የሚታወቅ ነው።

ባለፈው ነሐሴ ወር ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው የተሰጡት የኦብነግ የአመራር አባል ህግ-ወጥ እንደነበረ የሶማሊያ ፖርላማ አስታወቀ

የሶማሊያ የፓርላማ ኮሚሽን ባለፈው ነሐሴ ወር ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው የተሰጡት የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴና ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር አባል አቶ አብዲከሪም ሙሴ በህገ-ወጥ መንገድ መሆኑን ትናንት ቅዳሜ አስታወቀ።ፓርላማው ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በሗላ አቶ አብዲከሪምን  የሶማሊያ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ከህግ ውጭ አሳልፎ እንደሰጣቸው ትናንት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።ፓርላማው በተጨማሪም አብነግ ሽብርተኛ ድርጅት አለመሆኑንም ጠቅሷል።አቶ አብዲከሪም ሙሴን በህገ-ወጥ መንገድ ለኢትዮጵያ መንግሰት አሳልፎ የሰጠው የሶማሊያ ብሄራዊ መረጃና የደህንነት ኤጀንሲውን ጥፋተኛ አድርጓል።የብሄራዊ ደህንነት መስሪያ ቤቱ በተሳሳተ መረጃ ተመርኩዞ ሰውየውን አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግስት ከመስጠቱ በፊትም ለፍትህ አካላት ጉዳዩን ማሳወቅ እንደነበረበት ፓርላማው አክሎ ገልጿል።

  አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ፌርማጆ የሶሚሊያ ዜጋቸውን የጦስ ዶሮ ያደረጉት ከኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ድጋፍ በመሻት ነው የሚሉ አስተያየቶች በርካታ ሆነዋል። ኦብነግ በ1973 ዓ.ም አካባቢ እንደተመሰረተና ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚታገል ቡድን ሲሆን  የአመራር አባሉ ባለፈው ነሐሴ ወር በኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላን ከሶማሊያ ተወስደው  በደብረ ዘይት አየር ሀይል ግቢ ውስጥ መታሰራቸው ይታወቃል።በወቅቱ ኢትዮጵያም ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ሶማሊያዊያን እስረኞችን አሳልፋ መስጠቷም መዘገቡ ይታወሳል።ለእለቱ የያዝናቸው ዜናዎች እነዚህ ነበሩ ከቀሪ ዝግጅቶቻችን ጋር መልካም ቆይታ

 

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s