ዜና

Zemera Radio Weekly News 12,Nov,2017

 ሰላም ጤና ይስጥልኝ የተከበራችሁ አድማጮቻችን ከዘመራ ራዲዮ የአክብሮት ሰላምታችን ይድረሳችሁ!!የዘመራ ራዲዮ ሳምንታዊ ዜናስለምታዳምጡን እናመስግናለን!!መልካም ሰንበት

ኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ ያሰፍናል የተባለ አዲስ እቅድ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አወጣ

 የካንሰር በሽታ በአፍሪካ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተነገረ  ወደ ዝርዝሩ እንሄዳለን

 

የኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ ያሰፍናል የተባለ አዲስ እቅድ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አወጣ

የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ  ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች አርብ እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤ ስብሰባ  ካካሄዱ በሗላ የሀገሪቱን ሰላም ያሰፍናል ያሉትን አዲስ እቅድ ማዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጂ ፈርጌሳ በዝግ ስለተደረገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡ ሲሆን የሀገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ሲባል በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ሰልፎችን የጸጥታ ሀይሎች እንዲያስቆሙ ይደረጋል ብለዋል። በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደየ መጡበት ለመመለስ የጸጥታ ሀይሉ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነውም ብለዋል።ለግጭቱ ምክንያት የነበሩ የመንግስት አካላትና ግለሰቦች አስፈላጊው መጣራት ከተደረገ በሗላ ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ ሲሉም ዝተዋል።እንደ አቶ ሲራጅ ገለጻ አዲሱ እቅድ ለአንድ ዓመት ተግባራዊ የሚደረግና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ባለፈው ሐምሌ ወር ለአስር ወራት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህወሀት  ምክር ቤት ሲነሳ በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኗል፣ ከእንግዲህ ኮሽ የሚል ነገር የለም በማለት በልበ-ሙሉነት ተናግረው ነበር።ይሁንና አዋጁ ከመነሳቱ ሳምንታት በሗላ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈበት ተቃውሞ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን አሁን የወጣው አዲስ እቅድም አስቸኳይ አዋጁን በጓሮ በር እንዳመጡት በርካታ አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል።

  የካንሰር በሽታ በአፍሪካ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተነገረ

የዓለም የጤና ድርጅት ሐሙስ እለት ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው  በአፍሪካ የካንሰር በሽታ እያደገና አሳሳቢ እየሆነ እንደ መጣ ገለጸ። እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መግለጫ ከሆነ አህጉሪቱ ውስጥ እ.ኤ.አ በ2030 ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ከሚሞቱ አራት ሕሙማን ሦስቱ በካንሰር ይሆናል ሲል ስጋቱን ገልጿል። በአህጉሩ ለካንሰርን በሽታ ጥራት ያለው ህክምና መስጠት አለመቻሉ ችግሩን የበለጠ ውስብስና አስቸጋሪ እንዳደረገው ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።በፍጥነት እያደገ ላለው ለዚህ የጤና ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት ሁለት ግዙፍ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ከአሜሪካ የካንሰር ማኅበረሠብ እና ከክሊንተን የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ዩጋንዳን ጨምሮ ለሥድስት የአፍሪካ ሃገሮች የካንሰር መድሃኒቶችን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ  መስማማታቸውን ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።የካንሰር መድሃኒቶችን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ቃል ከተገባላቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ናይጄሪያ መሆናቸው ታውቋል ፡፡

የጣልያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለግራዚያኒ ሃውልት ያቆሙና መሬት የሰጡ ከንቲባን በእስራት እንዲቀጡ ወሰነ

እ.ኤ.አ በ2012 ከሮም ከተማ በስተ ምስራቅ ሀምሳ ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የአፊሌ ከተማ “አባትነት” እና “ክብር” የሚሉ መጠሪያዎች ተሰጥተውት በ160 ሺህ ዶላር ወጪ ለግራዚያኒ ሃውልት መቆሙን ተከትሎ የጣሊያን ፍርድ ቤት ድርጊቱ ተገቢ አይደለም በማለት በስራው  የተሳተፉትን የመንግስት አካላትንና ግለሰቦችን  በእስራትና በገንዘብ መቅጣቱ ተገለጸ። የመታሰቢያ ሃውልቱን እንዲቆም አድርገዋል የተባሉት የአፊሌ ከተማ ከንቲባ ላይ የስምንት ወራት እስራትና የ120 ዩሮ ቅጣት ሲጥልባቸው ሐውልቱ እንዲቆም አስተዋጽዖ አድርገዋል የተባሉ  ሁለት የምክር ቤት አባላት እያንዳንዳቸው የስድስት ወራት ጽኑ እስራትና የ80 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት ፍርድ ቤቱ እንደወሰነባቸው የሀገሪቱ የሚዲያ ተቋማት ዘግበዋል፡፡በሌላ በኩል ተከሳሾቹ የሰሩት ጥፋት ትልቅ በመሆኑ ተከሳሾቹ  ለአምስት ዓመታት የሚቆይ በማንኛውም የመንግስት ስራ ውስጥ ገብተው እንዳይሰሩ እገዳ ፍርድ ቤቱ እንደጣለባቸው ታውቋል።

 ግራዚያኒ የካቲት 12 ቀን 1928 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብን በአንድ ጀንበር ከ 30 ሺህ ሰው በላይ ያስጨፈጨፈ፤በአጠቃላይ የአምስት ዓመት ቆይታውም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ኢትዮጵያዊያንን የገደለና በሺህዎች የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት እንዱሁም ገዳማትን ያወደመ እጅግ ጨካኝ የነበረ ሰው ነው።

ከሼህ መሀመድ አላሙዲ እስራት ጀርባ የግብጽ እጅ እንዳለበት ህወሓት እንደሚያምን ተገለጸ

ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ሳምንት በሙስና ጠርጥራ ያሰረቻቸው ከፍተኛ ባለስልጣናትንና ባለሀብቶችን ገንዘብና  ንብረት እንደምትወርስ ሐሙስ እለት አስታወቀች፡፡ሳውዲ የባለሀብቶችንና ባለስልጣናትን ንብረቶች መቼና እንዴት እንደምትወርስ ዝርዝር መረጃ ባትሰጥም እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ  ግን 1‚700 የባንክ ሂሳቦች ታግደዋል።

በአልጋወራሽ ልዑል በመሐመድ ቢን ሰልማን የሚመራው የጸረ ሙስና ኮሚቴ ሀገሪቱ በሙስና ያጣችውን ገቢ ለማስመለስ የሚሞክር ከሆነ መጠኑ ወደ 800 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚሆን በሪያድ የንግድ ምክር ቤት አንድ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ጥናት ቢሮ ባደረገው ጥናት መሰረት ግብር ላለመክፈል ሲባል በሚሸሸግባቸው ሀገሮች ያለው የሳዑዲዎች ሀብት ከ300 ቢሊዮን ዶላር እንደሚልቅ ጠቁሟል።ሳዑዲ አረቢያ በቁጥጥር ስር ካዋለቻቸው  200 መቶ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች መካከል የ10.4 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ባለቤት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ አንዱ ናቸው።ሼህ መሀመድ አላሙዲ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያለቸው ሲሆኑ በግንባታ፣ ግብርና፣ማዕድን ማውጣትና የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለጸጋ ናቸው።ሼህ መሀመድ አላሙዲ ለህወሓት ባለቸው ቅርበት የተነሳ ከኢትዮጵያ ህዝብ ልብ እንብዛም የገቡ እንዳልሆኑም ይነገራል። የሳውዲ ዜግነት ያላቸው አላሙዲ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሳውዲ መዲና ሪያድ ሲያዙ የህወሓት መንግስት ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተልና የዲፕሎማሲ ስራም እንደሚሰራ አቶ ሀይለማርያም አስታውቀው ነበር።መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ  ከሼህ መሀመድ አላሙዲ እስራት ጀርባ የግብጽ እጅ እንዳለበት ህወሓት እንደሚያምን ተጠቅሷል።የግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ አልተባበር ብላች፤ለኢትዮጵያ ውሀ የልማት ጥያቄ ነው ለእኛ ደግሞ የህልውና የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው በማለት ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ማስጠቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለዛሬ ያልናቸው ዜናዎች እነዚህ ነበሩ መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ!!

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s