ፖለቲካ

ዘረኝነት ይጥፋ!! አርሴማ መድህኑ

 እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሃገራችን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እና አስጨናቂ  ላይ ደርስዋል። በተለይም ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ መያዣና መጨበጫው ጠፍቶት በመፈረካከስ ላይ ይገኛል።ኢትዮጵያ ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ  ወድ ልጆችዋ ለነፃነት፣ እና ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሲሉ ባደረጉት ትግል በስልጣን ጥመኞች በጥይት ግንባራቸው ተፍርክሶ፣በዘይት ተጠብሰው፣ጀርባቸው እስኪላጥ ተገርፈው፣ጥርሳቸው እረግፎ፣ አይናቸው እየጠፋ፣ ጥፍራቸው እየተነቀለ   በብዙ መከራና ስቃይ ህይወታቸውን ገብረውላታል። ሆኖም ግን  ይህ ሁሉ የተከፈለው ምስዋእትነት ኢትዮጵያን ወደ መረጋጋትና ወደ ስልጣኔ ያመራት ሳይሆን፣ የባሰውን ወደ መከፋፈል በሔራዊ ነጻነታችን ወደ መደፈር፣ዜጎችዋም ወደማያባራ ስቃይ መከራና ጭቆና ውስጥ ገብተው እናቶች በየዘመኑ በሚነሱ አምባገነኖች የልጆቻቸውን ህይወት እየገበሩ ወጣቶች በየበረሃው እና በየባህሩ ያለ ቀባሪ እየቀሩ ይገኛሉ።  ኢትዮጵያ ህዝቦቿ ከድህነት ተላቀው ዲሞክራሲያዊ ህይወት እየኖሩ የበለጸገችና የጠነከረች አገር ለመገንባት የምትችለው መቼ ነው? ይህ የሁላችንም ጥያቄ መሆን አለበት

ባለፉት 26  ዓመታት የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ችግር የጎሰኝነት አገዛዝ ስርዓት ነው፡፡ ይህ የጎሳ አገዛዝ ስርዓት ተጸንሶ ያደገው በህወሀት ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ውድመትን እና ጥፋትን ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋዕፆ አድርጓል። ህወሀት ስልጣንን በብቸኝነት ጨምድዶ ለመያዝ እና የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት እርሱ እና ተባባሪዎቹ ብቻ ማግበስበስ እንዲችሉ በማሰብ የጎሳ ስርዓት መስመርን በመዘርጋት ህዝብን ከህዝብ እና ጎሳን ከጎሳ ሲያፋጅ ኖርዋል። አሁንም እየታየ ነው፡፡ነገር ግን ህወሃት የለኮሰውን እሳት እያራገብን በአንድነት ተነስተን አገር መገንባትና የተከበረች አገር ጥሎ ከማለፍ ይልቅ እርስ በእርስ በመከፋፈል ዛሬ ለምናያት ኢትዮጵያ የየበኩላችንን አስተዋፅዖ አደረግን።

ህወሃት የተነሳበትን አላማ ሁላችንም የምናውቀው በመሆኑ ይህንን የዘረኝነት መንፈስ መስበር የምንችለው እኛው እራሳችን ነን። ከከፋፈለን አገዛዝ መጠበቅ የለብንም በግላችን ዘረኝነትን መጸየፍ እና መዋጋት አለብን እኔ በግሌ ኢትዮጵያዊ ነኝ። አገሬም ኢትዮጵያ ነች እዚያች አገር ተወልጃለሁ። ሰሜንም ደቡብም ምስራቅም ምዕራብም የኔ ነው የአገሬ  ጆግራፊያውዊ አቀማመጥ እኔን ይወክለኛል በኢትዮጵያዊነቴ ሰሜን ከጎደለች እኔም ጎድያለሁ ደቡብ ከጎደለ እኔም ጎድያለሁ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነቴ ሙሉ የሚሆነው ሰሜኑም ደቡቡም ምስራቁም ምዕራቡም የኔ ሲሆን ብቻ ነው ኦሮሞውም፣ ትግሬውም፣ ቤንሻጉሉም፣አፋሩም፣ሲዳማውም፣ ጉራጌውም የኔ ደሜ ነው ተሳስረናል ተጋብተናል   ተዋልደናል እንዴት ደሜን እረሳለሁ እንዴትስ ደሜን አፈሳለሁ   ሰሜንም ደቡብም ምእራብም ምስራቅም አድጌያለሁ። አብሮ አደግ ጓደኞቼ ከሁሉም አካባቢ የመጡ ነበሩ። ሁላችንም በአንድ ላይ ስንማር ስንጫወት  በሚያግባባን ቋንቋ እናወራለን። አፈር ፈጭተን  ጭቃ አቡክተን ያደግን እኩያሞች ሁሉ ለመጫወት የቋንቋ ምርጫ አልነበረንም። በዚህ ቋንቋዋ እንግባባ ብለን የወሰነውም ነገር የለም በምናውቀው ተግባባን፣ተጫውተን ተምረን አድገን እዚህ ደርሰናል። ዛሬም ከያለንበት በተለያዪ ቴክኖሎጂዎች ስንገናኝ በልጅነታችን ያሳለፍነውን እናውራዋለን እንስቃለን በትዝታ የኋሊት ፈርጥጠን ኢትዮጵያዊነታችንን እናቀነቅናለን የምን ዘረኝነት ከቶም አናውቀውም!!

ዘረኝነት ለኢትዮጵያችን አዲስ ክስተት ነው።ዘረኝነት ወይንም የዘርመድልዎ “….ዓላማው ወይም ውጤቱ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን በፓለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በባህላዊ ወይም በሌላ ማናቸውም የማኅበራዊ ህይወት ዘርፍ ውስጥ በእኩል መጠቀምን የሚያጠፋ ወይም የሚያሰናከል፤ በዘር፣ በቆዳ ቀለም፣ በአስተሳሰብ፣ በትውልድ ሃረግ፣ በጎሳም ይሁን በብሄር መነሻነት የሚደረግ አድልዖ፣ ማግለል፣ መከልከል ወይም የተለየ አሰራርን መጠቀም ነው።”

ስለዚህ ዘረኝነትን መጠየፍ እና መዋጋት ከኛ ከዜጎችዋ ይጠበቃል የዘረኝነት ጦስ የተረፈን ለኛው ነው። በዘረኝነት የተነሳ የስንቶች ቤት ፈረሰ ስንቶች እንደበግ ታረዱ ስንቶችስ መከራ እና ግፍ ተቀበሉ የዚህ ሁሉ ተጠያቂ ሀወሃት ብቻ ሳይሆን ከሱ እየተቀበልን የምናስተጋባ  ሁሉ የነጹሃን ደም በጃችን ነው። ዘረኝነታችን ካልቆመ መከራ እና ግፉ ደም መፋሰስ እና መመሰቃቀሉ አይቆምም።

ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔር ውጤት ናት ኢትዮጵያዊነት አብሮነት ነው።በዘረኝነት የመጣ ጣጣ ከምንሸከመው በላይ ሆኖ ጫንቃችን ላይ ተጥሎብናል። እያንዳንዳችን ለችግሩ መፍትሄ ፈላጊ እንጂ ችግሩን የምናባብስ መሆን የለብንም። ኢትዮጵያን ካልን ዘረኝነትን እንዋጋ ለኢትዮጵያ የደሙላት የቆሰሉላት ብሎም የተሰዉላት ዜጎች ሁሉ ለነጻነትዋ እና ለአንድነትዋ ነው። የኢትዮጵያን አንድነት ለመናድ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ዘረኝነት ነው የዘረኝነት አራማጆች ወደአንድ ቤተዘመድ ተጠቃለው በተቃራኒው  የኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ ላይ ሲዝናኑ እያዩ መታገስ ይበቃል።

ዘረኛው ቡድን ህወሃት የከፋፈላቸው እና ጦር ያማዘዛቸው  የአማራና የኦሮሞ ወንድማማች ህዝቦች ሰሞኑን ዳግም በመገናኘታቸው  በከፍተኛ ሁኔታ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን እያስተዋልን ነው። ስለዚህ ሴራው እየተንኮታኮተ ያለውን ዘረኛ አገዛዝ  በጋራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስሩ መንግሎ ለመጣል የኛ መተባበር እና ዘረኝነትን በመቃወም በትብብር መነሳት የግድ ይላል። የህወሃትን ሴራ ማክሸፊያ ጊዜው አሁን እና አሁን ብቻ ነው

የኢትዮጵያ ህዝብ የጠላቶቹን ክፉ ምኞት አምክኖ የቆየውን አንድነቱን አድሶ ተባብሮ እና እጅ ለእጅ ተያይዞ ሃገሩን ማዳን ግዴታው ነው። የመኖር ህልውናውም የሚከበረ ያኔ ነው። የከፋፋዮች ሴራ ማስፈጸምያ መሆኑ ቀርቶ ሴራቸውን የሚያከሽፈው እና የሚያሸንፈው በአንድነት መቆም ብቻ ነው። ያለፈውን ስህተት አርሞ ከጉድለቱ ተምሮ ህወሃት የሚያፈሰውን የህዝባችንን ነጹህ ደም ለማቆም የጋራ ትግሉን መቀጠል አለበት። እናም ልዪነታችንን  ወደጎን በመተው ስንቆም የነጻነት ቀናችን በቅርቡ እንደሚሆን አልጠራጥርም!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

 

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s