ዜና

Zemera Radio Weekly News 05,Oct,2017

የአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች የምክክር መድረክ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሄደ

አዲሱ የአሰሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ  የባርነት አዋጅ ነው በማለት የቀድሞው የኢሰማህኮ መሪዎች አወገዙት

በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የ14 ቀን ጸሎተ ምህላ እንዲታወጅ ወሰነ

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፈው ማክሰኞ  ምልዓተ-ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስለ ተከሰተው ግጭትና ስለደረሰው ጉዳት በመነጋገር፤ ከነገ ሰኞ ጀምሮ ለ14 ቀናት ጸሎተ ምህላ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ገዳማትና አድባራት እንዲካሄድ ወሰነ። ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሠተው ግጭት በአስቸኳይ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍንም ለማድረግ ከመንግስት ጋር ውይይት እንዲደረግ እንደሚሰራ የሲኖደሱ መግለጫ ያመለክታል።በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖችም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባለው መዋቅር  የስድስት ሚሊዮን  ብር ድጋፍ እንዲደረግ  ሲኖዶሱ መስማማቱ ታውቋል። የኢትዮጵያ ህዝብ የመቻቻል፣መከባበር፣ መደማመጥና የመግባባት መንፈስን በማጎልበት በአንድነት ተባብሮ  እንዲኖርም ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጸሎተ ምህላ እንዲካሄድ ማወጇን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በገፍ ሲገደልና ሲታሰር የመንግስት አጋር በመሆን የህዝብን ሰቆቃ በዝምታ ማለፏን በመጠቀስ አሁን የሚደረገው ጸሎተ ምህላ በቤተክርስቲያኗ ዶግማና ቀኖና ሳይሆን በመንግስት ይሁንታ ላይ የተመሰረተ ነው በማለት አንዳንድ ወገኖች ትዝብታቸውን እያካፈሉ ነው። የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ የኢህአዴግ አምባገነናዊ የአገዛዝ ስርዓት በዜጎች ላይ የፈጸመውን የጅምላ ግድያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዝምታ ማለፏ የሚታወስ ነው።

የአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች የምክክር መድረክ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሄደ

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የተመራ የልዑካን ቡድን  ትናንት በባህር ዳር ከተማ በመገኘት ከአማራ ክልል መንግስትና ከ1500 ከሚልቅ ህዝብ ጋር ምክክር ተካሄደ። የምክክር መድረኩም አብሮነታችን ለሰላማችን ፣ሰላማችን ለአብሮነታችን በሚል መሪ ሀሳብ እንደሆነም ታውቋል። የኦሮሚያ የልዑካን ቡድኑ ከመንግስት አካላት፣ከአባ ገዳዎች፣ሙህራንና ከአርቲስቶች የተውጣጡ ከ250 በላይ ሰዎችን ያካተተ ሲሆን አርብ እለት ወደ ባህር ዳር ሲያመራ ደጀን ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።የባህር ዳር ከተማ ወጣቶችም አቶ ለማ መገርሳ ወደ ባህር ዳር እንደሚመጡ በሰሙ ጊዜ “ከሁለት ሳምንት በፊት የእንቦጭን አረም ለማስወገድ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ  ከ200 በላይ ወንድሞቻችንን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን በደስታ ተቀብለን አስተናግደን፤ ላደረጉልን ወንድማዊ ድጋፍ ከልብ አመስግነን በሰላም ግቡ ብለን ሸኝተናቸዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ አባ ገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በክብር ተቀብለን ለማስተናገድ ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።በምክክር መድረኩ ምሁራን የሁለቱ ጎሳዎችን የቆየ የዘመናት ግንኙነትን በተመለከተ ጥናታዊ ጹሁፍ አቅርበዋል።መድረኩ የአማራንና ኦሮሞን ህዝብ የበለጠ ለማስተሳሰር ጠቃሚ እንደሚሆንም አስተያየት እየተሰጠ ሲሆን የሁለቱ ክልሎች የኮሚኒኬሽን ሀላፊዎች እንዲህ አይነቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።የኦሮሚያ ክልል የወቅቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ከሁለት ዓመታት በፊት በክልሉ በተፈጠረው ህዝባዊ እቢተኝነት እየተፋፋመ በመምጣቱ  የአቶ ሙክታር ከድር አስተዳድርን በማፍረስ ከአንድ ዓመት ፊት መንበረ-ስልጣኑን ከጨበጡ ወዲህ በህዝብ ዘንድ የአንድነት አቀንቃኝና በህወሓት ላይ ያመጹ እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራል።አቶ ለማ መገርሳ የኢትዮጵን ህዝብ በማስገደልና በማሳሰር ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው በሚባለው ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል።የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ወዲህ ደግሞ የህወሓት ባለስልጣናትን የማያስደስት ከተለመደው አካሄድና አሰራር ወጣ በማለት  በየ መድረኩ በድፍረት ሲናገሩ ይደመጣሉ።እሳቸው የሚመሩት ኦ.ህ.ዴ.ድም ስለ “ኢትዮጵያ አንድነት” በማቀንቀኑና የህወሓት አባላት በኦሮሚያ ክልል እንደፈለጉ  መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው በግልጽ የሚታይ አለመግባባት እንደተፈጠረ የሚያመላክቱ በርካታ ምልክቶች ይስተዋላሉ።የፓርላማው አፈ-ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ “ህዝቤና ድርጅቴ ክብሩ ተነክቷል” በማለት ከሀላፊነታቸው ለመልቀቅ እንደወሰኑ ባለፈው ወር በይፋ መግለፃቸውም የሚታወቅ ነው። የአሁኑ የፕሬዚዳንቱ  የባህር ዳር ጉዞ ዓላማ ከአማራ ህዝብና ከብሄረ አማራ ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጋር ያለውን የወዳጅነት መንፈስ የበለጠ ለማጎልበት ሊሆን እንደሚችልና ይህም ለ26 ዓመታት ሀገሪቱን በበላይነት ሲገዛ ለኖረው ህወሓት መልካም ዜና ሊሆን እንደማይችል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

አዲሱ የአሰሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ  የባርነት አዋጅ ነው በማለት የቀድሞው የኢሰማህኮ መሪዎች አወገዙት

   በስደት የሚገኙ የሠራተኛ መሪዎች ባለፈው ሰኞ ባወጡት መግለጫ በአዲሱ  የሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ ሥም በሃይል ሊጫን የታሰበው የባርነት አዋጅ ነው በማለት በጽኑ ተቃወሙት። ሰራተኛው አዲሱን  ረቂቅ አዋጅ ለመቃወም የስራ ማቆም አድማ ማድረግ አለማቀፋዊ መብቱ ቢሆንም በሀገር ወስጥ ያሉት የሰራተኛ ማህበራት ባለልጣናት የሠራተኛውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚበቃ ሰብዕናም ሆነ ታሪክ የሌላቸው ካድሬዎች መሆናቸውን  በስደት የሚገኘው የቀድሞው የሰራተኛ ማህበራት አመራሮች ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። ሰራተኛው በሥርዓቱ ላይ እንዳያምጽ ከማባበልና ለሥርዓቱ የመተንፈሻ ጊዜ ለማስገኘት የይስሙላ መግለጫ ከማውጣት አልፈው አሁን በኮንፌዴሬሽኑ አመራር ላይ ያሉት የሕወሃት ተሿሚዎች ከፈጣሪያቸው ህወሓት ጋር በቁርጠኝነት ይታገላሉ ብሎ ሰራተኛው እንዳይታለልም  ምክራቸውን ለግሰዋል።ሰራተኛው በዘር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ መስመር ሳይከፋፈል  በጋራ በመቆም መደባዊ ጥቅሙን ለማስከበር ትግሉን እንዲያጠናክር መሪዎቹ ጥሪ ያቀርባሉ።፡አዲሱ የሰራተኛ ረቂቅ አዋጅ አለም አቀፋዊ የሰራተኞችን መብት የሚጎዳና የኢንዱስትሪ ሰላምን የሚያናጋ ነው በማለት ከተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል።በረቂቅ አዋጁ ላይ አንድ ሰራተኛ በወር ውስጥ ሁለት ቀን ካረፈደ አልያም በስድት ወር ወስጥ አምስት ቀን ከቀረ አሰሪው ያለማስጠቀቂያ የስራ ውል ማቋረጥ እንደሚችል ይደነግጋል። የቀደመው የሰራተኛ አዋጅ  አንድ ሰራተኛ በተከታታይ አምስት ቀን ወይም በወር ውስጥ 10 ቀናት አልያም በዓመት ውስጥ 30 ቀናት በስራ ገበታው ካልተገኘ አሰሪው የስራ ውል ማቋረጥ እንደሚችል ይደነግግ ነበር።አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የሀገሪቱን የትራንስፖርት እጦት ያላገናዘበ በመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት በርካታ አሳቦች እየተሰነዘሩ ነው።

በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ

የፌደራል አቃቤ ህግ በኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ አርብ  ጥቅምት 24/2010 ዓም ሁለት ምስክሮች አሰምቷል። ሁለቱም ምስክሮች ታህሳስ 14/2009 ዶር መረራ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከኮምፒውተር የወጣን ፅሁፍ የእራሴ ነው ብለው ሲፈርሙ ተገኝተን ታዝበናል ያሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። የአቃቤ ህግ አንደኛ ምስክር ማዕከላዊ የሄደበትን ምክንያት ሲጠየቅ  ዘመድ ሊጠይቅ መሄዱን፣ ብቻዬን ከምሄድ በሚል ሁለተኛ ምስክርን አብሮኝ  እንዲሄድ ጠይቄው ከምንሰራበት መስሪያ ቤት አብረው እንደሄዱና  ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ጠይቋቸው እንደተስማሙ ገልፆአል።በሌላ በኩል ሁለተኛ ምስክር  ከአንደኛ ምስክር  ጋር አንድ ክፍለ ከተማ እንጅ አንድ መስርያ ቤት እንደማይሰሩ፣ ብቻውን በመስርያ ቤት ትዕዛዝ ለመርማሪዎች ሰነድ ለመስጠት እንደሄደ፣ ስራውን ጨርሶ ከመርማሪው ቢሮ ሲወጣ ኮማንደር አሰፋ በተባለ የምርመራ ክፍል ሀላፊ እማኝ እንዲሆን መጠየቁን፣ እሱ ስራዉን ጨርሶ ከወጣ እና እማኝ ለመሆን ፈቃደኛ ከሆነ በኋላ አንደኛ ምስክር የሆነውን ሰው እንዳገኘው የተዋወቁትም በማዕከላዊ እማኝ ከሆነ በሗላ ነው ሲል ለችሎት አስረድቷል። በተጨማሪም አንደኛ ምስክር በወቅቱ ዶ/ር መረራ ሹራብ ለብሰው ነበር ሲል ሁለተኛ ምስክር ጅንስ ሱሪና ጅንስ ሸሚዝ ለብሰው ነበር ብሏል። በዶ/ር መረራ ላይ ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ሌሎች ሁለት ምስክሮችን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳላገኛቸው የገለፀ ሲሆን ሁለቱን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 21/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። ባለፈው ሳምንት በርካታ የፍርድ ቤት ችሎቶች የነበሩ ሰሆን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለአቶ በቀለ ገርባ ፈቅዶ የነበረው የ30 ሺህ ብር ዋስትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት አግዷል።አጣሪ ችሎቱ ዋስትናውን ያገደው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቤቱታን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።ስለ ጉዳዩ አስስተያየታቸውን እንዲያካፉሉን የአነጋገርናቸው  አንድ  የህግ ባለሙያ “ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት” የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ መሻር እንደማይችል  አስተያየታቸውን ሰተውናል።የሰበር ሰሚ ችሎት ስልጣን የጠቅላይ ፈርድ ቤት ውሳኔዎችን በመመርመር  አስተያየት መስጠት እንጂ መሻር አይችልም ብለዋል።የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በእስር ቤት ሀላፊዎችና በመንግስት ባለስልጣናት ሲሻር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።በተለይም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቁ ውሳኔ ሲያሳልፍም ለወራት በእስር ቤቶች እንዲያሳልፉ እንደሚደረግ የሚታወቅ ነው።

 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ጥቅምት 30 ሊያደርግ የነበረውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊፋ ታገደ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥቅምት 30/2010ዓ.ም ሊያደርግ  የነበረው ፕሬዚዳንታዊ  ምርጫ በፊፋ መታገዱን ሪፖርተር የእግሊዝኛው ክፍል አርብ እለት ዘገበ። ምርጫው የታገደውም የፊፋን የ”ምርጫ መርሆዎች” ያማሏ ባለመሆኑ እንደሆነ ተጠቅሷል።አሁን ባለው የፌዴሬሽኑ አሰራር ለምርጫ የቀረቡ ተወዳዳሪዎች ያቀረቡት ማመልከቻን የሚመረምረው በጠቅላላ ጉባኤ በተመረጠው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሲሆን ከመረመረ በኋላ ለምርጫ ኮሚቴው ያቀርባል፡፡ይህ ደግሞ ከፊፋ የአስተዳደር መርህ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ አሰራሩ መሻሻል ይኖርበታል ሲል  ፊፋ በጥብቅ አስገንዝቧል፡፡በመሆኑም ጥቅምት 30 የሚደረገው ምርጫ በፊፋ ድጋፍ የምርጫ ኮሚቴ እና አስፈላጊ የምርጫ መስፈርቶች ተሟልተው ለፊፋ እስኪቀርቡ ድረስ እንዲራዘም ማሳሰቡን የፊፋ ዋና ጸኃፊ በፋትማ ሳሞራ የተጻፈው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ለጥቅምት 30/2010ዓ.ም ሊካሄድ በነበረው ምርጫ አምስት ተወዳዳሪዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን አቶ ተካ አስፋው፣ ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣አቶ አንተነህ ፈለቀና አቶ ዳግም ሀግኖክ ነበሩ።

 

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s