ፖለቲካ

የዱላ ቅብብሎሽ….. ከደረጄ ነጋሽ

ጥቅምት 23ቀን 2010 ዓም(02-11-2017)

ከተለያዩ የእስፖርት ውድድሮች ውስጥ አንዱና ማራኪ የሆነው  በተወሰነ የርቀት እሩጫ  በቡድኖች መካከል ዱላ እየተቀባበሉ የሚያካሂዱት ውድድር ነው።በዚያ ውድድር ላይ ፈጣንና ጠንካራ የተባሉት ተመርጠው ይሰለፋሉ፤ፍጥነትና ጥንካሬያቸው ግን ለተወሰነ እርቀት ታስቦ ነው።በዚያ ውድድር ላይ ደክሞት ወይም የሚቀባበለው ዱላ ከእጁ አምልጦት ሲወድቅበት ለማንሳትና ለመቅደም የሚውተረተር አይጠፋም። ምንም ጊዜ ቢሆን መሸነፉን አምኖ ከጨዋታው ሜዳ አይወጣም።የአንዱ ድክመት በሌላው አጋሩ እየተሸፈነ እስከ ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ድረስ  ውድድሩ ይቀጥላል። ተወዳዳሪዎቹ ሁሉም የሰለጠኑት በዱላ ውድድር ስለሆነ ዱላዋን ጨብጦ መሮጥ ግዴታቸው ነው።ካለ ዱላዋ ከጨዋታው ሊካፈሉ አይችሉም። ሁሉም የዱላ እስፖርተኞች ወይም አባዱላዎች ናቸው።በመጨረሻው በዱላ ቅብብሉ ውድድር ጠንካራ የሆነው አባ ዱላ ቡድን የሽልማቱ ባለቤት ይሆናል።

ይህንን በአገራችን የፖለቲካ ሜዳ ላይ ተርጉመን ስናዬው ተወዳዳሪዎቹ በዘርና  በጉልበት የሚያምኑ ቡድኖች ሲሆኑ  የፉክክሩ  ዓላማና ግብ  ለተወሰነ የስልጣን ዘመን የሚያበቃቸውን የስልጣን ዱላ ወይም በትረ-መንግሥት ለመጨበጥና የበላይ ሆኖ ለመኖር ነው።በዚህ የጎሳ ቡድኖች መካከል በሚደረገው ፉክክር ጠንካራና ደካማ ይኖራል፤እንደ ዱላ ቅብብሉ እስፖርት አንዱ በትረ-መንግሥቱ ከመዳፉ ሊያመልጠው የሚችልበት ሁኔታ  ሲኖር ያንን ተቀብሎ ተረኛ አባ ዱላ ለመሆን የሚበቃ ደግሞ ይኖራል።የዚያ ሽኩቻና ውድድር ግለት የሚፈጥረው ጠረን ሰሞኑን መሽተት ጀምሯል።

ላለፉት 27 ዓመታት አባ ዱላ ሆኖ ሲያፋጅ የኖረው የወያኔ መራሹ ቡድን  በሕዝብ ተቃውሞ በተለይም በኦሮሞውና በአማራው ማህበረሰብ በኩል በተነሳው እምቢተኛነት ጉልበቱ ዝሎና ተዳክሞ ለመውደቅ መንገዳገድ ሲጀምር፣ አጋሮቹ ሊያንሰራራ የሚችልበትን መንገድ ይዘው ብቅ ብለዋል።የሕዝቡን  ስነ-ልቦና  ለመስለብ የሚችል ቋንቋና መልእክት  የሚናገሩትን ወደ መድረኩ እንዲወጡ በማድረግ ለስርዓቱ መዳኛ ቀጭን የማርያም መንገድ ዘርግተዋል። በትግሉ ግለትና ስፋት የተነሳ በኦሮሞው ማህበረሰብ በኩል የተቀሰቀሰባቸውን አደጋ  የሚያዳክሙበትን ዘዴና ብልሃት ፈጥረዋል።ለዚያም የተመረጠው  የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራቲክ ድርጅት ወይም ኦሕዴድ(OPDO) የተባለውን እንደ ጎማ ቀይሮ ስርዓቱን  እንዲያሽከረክር ማድረግ  ነው።

ይህ ስልት በቅርቡ የተወጠነ ሳይሆን እንደ አማራጭ ሆኖ በይደር የተያዘ፣በምዕራቡ አገሮች ተባባሪነት የተዘጋጀ ወጥመድ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኦሕዴድ(OPDO) አባላት በተለያዩት የአውሮፓ አገሮች በተለይም ጀርመን፣ሆላንድ፣ስዊድን…ውስጥ የተለያዬ ስልጠና ሲከታተሉ ቆይተው መመለሳቸው ያደባባይ ምስጢር ነው።ይህንን ስልት ተግባራዊ ለማድረግ በውጭ አገርና በአገር ቤት ውስጥ በሚስጥርና በይፋ በመደራደር መልክ እንዲይዝ ጥረት ከማድረግ አልፎ ይፋ እየሆነ በመታዬት ላይ ነው።ከወያኔ ጋር የስርዓቱ አካል ሆኖ የኖረውን ድርጅት መሪ ከክልል ፕሬዚደንትነት አውጥቶ ጠ/ሚኒስትር ለማድረግ ወደ ሚቻልበት ደረጃ ለመድረስ የቀረው ጊዜ  አጭር ይመስላል፤ወሳኙ የሕዝቡ ትግል ሂደት ነው።ይህ ስልት ተግባራዊ ከሆነ ምናልባትም በኦሮሞው ማህበረሰብ በኩል የተነሳውን ተቃውሞ ለጊዜው ሊያስተነፍሰው ይችል ይሆናል እንጂ  የመጨረሻ መፍትሔ ሊሆን አይችልም።ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የግፉ ተጠያቂ ሆኖ የኖረው ኦሕዴድ በአንድ  ጀንበር ተገልብጦ ሕዝባዊ ስሜት ሊያድርበት አይችልም፣የተፈጥሮ ጸባዩም አይፈቅድለትም።ለወንጀሉ ሁሉ ተጠያቂ ነው።ጎሰኛ ጎሰኛ ነው፤ከጎሳው አጥር ውስጥ ወጥቶ ሰብአዊና ሕብረ ብሔራዊ ስሜት ሊያድርበት አይችልም።የተቀመረው አሻጥር ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመጽ ለማዳፈን የእሳት አደጋ ሆኖ እንዲያጠፋ የተደረገ የመጨረሻ ሙከራ ነው። በሚጎሰመው የውሸት ነጋሪትለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብና መጠበቅ ጅልነት ነው።ስርዓቱን ለማዳን የሚደረግ ማጭበርበ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።የኦሮሞን ወጣት እስከ አሁን ድረስ ያስጨፈጨፈው፣በሽህ የሚቆጠሩ ንጹሃንን በእስርቤት አጉሮ የሚያሰቃየው ማን ሆነና ነው የሕዝቡን ጩኸት ቀምቶ ደረት በመምታት ሙሾ ለማውረድ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚባለው?ለወደፊቱስ ላለመጨረሱ ምን ዋስትና አለው?የዘረ ፖለቲካና ዘረኝነት በሰፈነበት ስርዓት ውስጥ የመተላለቁ ዕድል የሰፋ ነው፤በዘር ፖለቲካ እምነትና የስልጣን ውጣ ውረድ በአንድ ወቅት ተጠቂ የነበረው በሌላ ወቅት አጥቂ ይሆናል።የሚመራበት” ተራዬ ነው” የሚለው የበቀል  ሕገ አራዊት ይሆናል። እንደ ዱላ ቅብብሉ እስፖርት የወያኔ የበላይነት በኦሮሞው ወይም በሌላው የበላይነት ቢተካ ለውጡ የጅራፍ ለውጥ ነው። ተወዳዳሪው ቢለዋወጥ የዱላ ቅብብሎሹን  የእስፖርት ጠባይ አይቀይረውም።ያው የዱላ ቅብብሎሽ እስፖርት ነው።የጎሳ ፖለቲካው ወይም ስርዓቱ  በጎሳ ድርጅቶች መካከል በሚደረገው የስልጣን ውጣ ውረድ ይዘቱን አይቀይርም።በአገራችን የፖለቲካ ሜዳም የወያኔ የበላይነት በኦሕዴድ፣በበአዴን  ወይም በደቡብ ሕዝቦች ድርጅት ቢቀየር ፤ የሃይለማርያም ደሳለኝ ጠ/ሚኒስትርነት  በለማ መገርሳ ቢለውጥ ያው የጉልቻ ለውጥ ከመሆን ያለፈ የስርዓት ለውጥ አይሆንም።ቀልቀሎ ስልቻ፣ስልቻ ቀልቀሎ!

የሕዝቡ ትግል  ሲጠናከር በገዢው ጎራ  በሚፈጥረው ስጋትና ጭንቅ አልፎ አልፎ እራስን ከተጠያቂነት ለማዳን የሚደረግ ሙከራና የእርስ በርስ መከዳዳትና ከደሙ ንጹህ ነኝ የማለት አዝማሚያ እየታዬ መጥቷል።ለስርዓቱ መፈረካከስ ቢረዳም፣ አንዱን ከሌላው ወይም ከነበረበት ወንጀለኛ  ቡድን  የተሻለ አድርጎ ለማዬት የሚያስችል አይሆንም።አልፎ ተርፎም በእርቅና መግባባት ስም  የተፈጸመ ወንጀል ተድበስብሶ የሕግ የበላይነት ተሽሮ ወንጀለኛ በሰራው ጥፋት ሳይጠየቅ የሚቀርበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርግ ሙከራ እየተስተዋለ መጥቷል።እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩና በባሕሉ ግጭትን በሰላም፣በደልን በይቅርታ መለወጡ አይካድም፤ግን አንተም ተው አንተም ተው፣ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን በማለት ብቻ ሳይሆን የበደለ በፈጸመው በደል  ተጸጽቶ የበደለውን ይቅርታ ሲጠይቅና ሲክስ፣የዘረፈውን ሲመልስ  ፣ለወደፊቱም መቀጣጫ እንዲሆን በሚያስችለው መንገድ ሊሆን ይገባዋል።ያ ካልሆነ ተመሳሳይ ጥፋትና ወንጀል እንዳይደገም የሚያግደው የለም።

የስርዓት ለውጥ የሚመጣው፣ሕዝቡም የሚታገልለት የአገራችን አንድነትና  የእኩልነት መብት የሚረጋገጠው፣ በጎሰኞች ስርዓት መቃብር ላይ በፍልስፍናና በእውቀት ላይ ያረፈ የፖለቲካ ራዕያ ያለው  ስርዓት ሲመሰረት ብቻ  እንጂ ጎሰኞች እየተቀባበሉ በሚመሩት ስርዓትና  በሚረጩት የዘር መርዝ የተጠቀለለ ፖለቲካ አይደለም። የሚታየው ስርዓቱን የማዳን እርብርቦሽ  ለሕዝቡ ችግርና ጥያቄ መልስና መፍትሔ ሊሆን አይችልም።መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያዊነት ጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ፣ሁሉንም ያሳተፈና የሁሉንም ተገቢ ጥያቄ በተገቢው መንገድ ሊመልስ የሚችል፣ከዘር ና ክልል አጥር የወጣ ፣ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ሲመሰረት ብቻ ነው። በመሆኑም  ለዚያ የቆሙ ሃይሎች አማራጭ ሆነው ሊቀርቡ ይገባል።በተቃዋሚ ስም በተመሳሳይ የጎሳ ፖለቲካ የተደራጁትን መደገፍና እንደ አንድነት ሃይል መቁጠር ውጤቱ ያው በገሌ ነው።ይህ ሁሉ ጣጣ የጎሳ ፖለቲካ የወለደው ችግር ነው።የጎሳ ፖለቲካ ካልተወገደ ከዚያ ችግርና ማጥ ውስጥ መውጣት አይቻልም።

በየቦታውና በየወቅቱ በአንድነት ስም ተደራጅቶ  በተናጠል መሯሯጥም   ለጥቃት አመቺ ያደርጋል፤አንድ ጠንካራ አማራጭ ሳይኖር ለወያኔና ተባባሪዎቹ ቀጣይ ስርዓት ይዳርጋል።በተደጋጋሚ የታየው የመጠላለፍ አባዜ በቃል ተቃዋሚ በተግባር ግን የስርዓቱ ደጋፊ ከመሆን የተለዬ አድራጎት አይደለም።

አሁን ከፊታችን የተደቀነውና  ጎልቶ የሚታየው የአገራችንን ህልውና የሚፈታተነውና ለመበታተን የሚያስችለው አደጋ ስለሆነ ያንን ለመቀልበስ በእውነት ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን  የሚታገሉት አገር ወዳዶች ጠንክረው መውጣት ይኖርባቸዋል።የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነት ወይም የግል ጥላቻና የስልጣን ሽኩቻ ለመለያየትና በአገር አድኑ ትግል ላለመሳተፍ እንቅፋትና ምክንያት ሊሆናቸው አይገባም።እኔ ብቻ የሚለው እብሪታዊና  የበላይነት ስሜት ለራስም እንደማይበጅ ሊታወቅ ይገባል። የመጨረሻ ውጤቱንም ከወያኔ ታሪክና አሁን ከደረሰበት ውድቀት አይቶ መማር ይቻላል።

የመጠላለፉና የውድድሩ ነገር በሰብአዊ ተግባር በሚደረገው ዘመቻም ላይ የታዬ ድክመት ነው።

ሰሞኑን በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጭፍጨፋና መፈናቀል ምክንያት በየፊናው እርዳታ ሲሰበሰብ ሰንብቷል።እርምጃው የሚነቀፍ አይደለም።ግን እንደ ፖለቲካው ትግል የእርስ በርስ ሽሚያና እሽቅድምድም የታዬበት ሆኗል። የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚህ ሰብአዊ ግዴታ ላይ መሳተፋቸው መልካም ቢሆንም፣እርዳታውን ትኩረትና እውቅና ለማግኘት መሳሪያ ለማድረግ  ሲሞክሩ ተስተውሏል። በግለሰቦችም ተነሳሽነት የተደረገ የገንዘብ ማሰባሰብ ሙከራ የሚናቅ አይደለም። የተሰበሰበው እርዳታ ለተጎጁ ወገን የሚያደርሱበት መንገድ ግልጽ ባለመሆኑና አልፎ ተርፎም እርዳታው በወያኔ ቁጥጥር ስር በወደቀው ባንክ በኩል መላኩ ሲታወቅ  ለመርዳት የሚፈልገውን ጥርጣሬ ውስጥ ከቶት የእርዳታው ተካፋይ እንዳይሆን  አድርጎታል።ይህንን የመሰለው ችግር ተደጋግሞ የተከሰተ ስለሆነ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል።መፍትሔውም አንድ አገራዊ የቀውስ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ የሆነ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ነጻ የሆነ፣ ሕጋዊነትና ግልጽነት ያለው፣ የሂሳብ ወጭና ገቢውን ይፋ የሚያደርግ፣በነጻ የሂሳብ ተቆጣጣሪዎች እይታ ስር የዋለ፣አላፊዎቹ በተወሰነ የአገልግሎት ጊዜ(ግፋ ቢል በየሁለት ዓመቱ) የሚለዋወጡበት የእርዳታ አስተባባሪ አካል መፍጠር ነው።በዚህ መልክ  የተቋቋመ ድርጅት መኖሩ ሰርገኛ መጣ ብሎ ከመሯሯጥ ያድናል፤እምነትም ይጣልበታል።በተራዘመ  ሂደት የተሻለ እርዳታ(Emergency Fund) ለመሰብሰብ የሚያስችል  አቅም ለመገንባት ይረዳል።ለዚህ ዓላማ የተፈጠረ ድርጅት ካለም ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች የሚያሟላ ሊሆን ይገባዋል። በአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባላትና ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር እንዳይወድቅ በንቃት መጠበቁና  መከላከሉ ተገቢ ነው።

የአምባ ገነኖችና የጎሰኞች በትረ-ስልጣን ቅብብሎሽ በኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት ክንድ ይሰበራል!

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!

አገሬ አዲስ

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s