Uncategorized

Zemera Radio Weekly News

 

 

በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው

በኦሮሚያ ክልል ዳግም ያገረሸው ህዝባዊ ተቃውሞ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። ህዝባዊ ተቃውሞው ጋብ ካለበት ባለፈው ሳምንት ዳግም በመቀስቀስ  በተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል። በሰሜን ሸዋ ዞን ከማክሰኞ ጀምሮ በጫንጮ፣ ገብረጉራቻና ጓሀጺዮን  በተካሄዱ ህዝባዊ  አመፆች በርካታ የመንግስት ተሽከርካሪዎችንና የባለስልጣናት ንብረቶች በእሳት ተቃጥለዋል።በአምቦ፤ በወለጋ፤ ጎሬ፣ መቱና በበደሌ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው  ህዝብ አደባባይ  በመውጣት የህወሃት የአገዛዝ ስርዓት እንዲወርድ ጠይቋል።በተቃውሞው ወቅትም ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎች ሲቃጠሉ ከ18 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም የሚወስደው አውራ ጎዳና በህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ተስተጓጉሎ እንደነበረ የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።የኦሮሚያ ፖሊስ በህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ህዝባዊ ወገንተኝነት አሳይተዋል ያላቸውን የጸጥታ አባላትን እያደነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚንኬሽን ቢሮ ሐሙስ እለት አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ከሌላ ቦታ የመጡ ግለሰቦች ሰላማዊ ሰልፎችን ወደ ግጭትና ብጥብጥ ለመቀየር ሰርተዋል ያላቸውን ከ100 በላይ ሰዎችን ማሰሩን ገልጿል። ህዝባዊ አመጹን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መካከለኛና የበታች አመራሮችን በስልጠና ስም የማዘናጊያ ፕሮፖጋንዳ ለመሙላት ለ45 ቀናት ወደ መቀሌ እንደሚያቀኑ መረጃዎች ወጥተዋል።

የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ማስገባታቸውን ቀጥለዋል ተባለ

የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ህዝባዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት የስርዓቱ ነባር ባለስልጣናት የመልቀቂያ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸው ታውቋል። የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ  ባለፈው ሳምንት ጥያቄ  ማቅረባቸውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ገልጿል።አቶ በረከት የሥራ መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ማቅረባቸው የታወቀ ሲሆን ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ ያደረሳቸው ምክንያት በግልፅ የተነገረ ነገር የለም።ብዙዎች እንደሚሉት አዲሱ የብአዴን አመራር ለአቶ በረከት እንደለመዱት ቆራጭ ፈላጭነታቸውን ስላልተቀበላቸውና በዚህም ተስፋ እንደቆረጡ በርካታ ጭምጭምታወች እየተሰሙ ነው። አቶ በረከት ስምኦን  ከቅድመ መለስ ዜናዊ ሞት በፊት ከእሳቸው ቀጥሎ የሀገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ እንደሆኑ የሚታመን ሲሆን ላለፉት 26 ዓመታት በሺህዎች የሚቆሩ ለበርካታ ኢትዮጵያን ሞት፣እስራትና ስደት ቀጥተኛ ምክንያት በመሆናቸው ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል። በኢትዮጵያ ታሪክ ወስጥ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ህዝቡ ቅንጅትን ቢመርጥም በጠመንጃ የህዝብ ድምፅ በመንጠቅ ከጓዳቸው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በመሆን የእርሳቸውን አገዛዝ አስቀጥለዋል። በኢትዮጵያ ጉዳይ አዘውትረው አስተያየት በመስጠት የሚታወቁትና በ1997 ዓ.ም የተደረገውን ምርጫ የአውሮፓ ህብረት የታዛቢዎችን በመምራት ኢትዮጵያ የተገኙት ወይዘሮ አና ጎሜዝ የአቶ በረከትን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ሲሰሙ “የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጩና ጨካኙ በረከት ስምኦን በህግ መጠየቅ አለባቸው” በማለት በቲዊተር ገፃቸው ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ በረከት ስምኦን ለበርካታ ዓመታት በቦርድ ሰብሳቢነት ሲመሩት ከነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም እንደለቀቁ ባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ዘግቧል።ቀደም ብሎም ባለፉት ሰባት ዓመታት የህዝብ ተወካዮች አፈ-ጉባኤ በመሆን የሰሩት አባ ዱላ ገመዳ ህዝቤና ድርጅቴ ተዋርዷል በማለት ከሀላፊነታቸው ለመልቀቅ እንደወሰኑ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ከሀላፊነቴ እለቃለሁ አሉ ተባለ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ስራዬን ለመስራት ተቸግሬያለሁ በማለት ስልጣን ለመልቀቅ መናገራቸውን የቤተክህነት ምንጮችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች አመለከቱ። ሐራ ተዋህዶ የተባለው በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው ድረገጽ እንደዘገበው ፓትሪያርኩ ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ በቃል ያሳወቁ ሲሆን በቀጣይም በጽሁፍ ያሳውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም ባለፉት 4 ቀናት በአዲስ አበባ በተካሄደው የቤተክርስቲያኒቱ 36ኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በዋሽንግተን የሚገኙትን አቡነ ፋኑኤልን ፓትሪያርኩ መወረፋቸው ይፋ ሆኗል። ላለፉት አምስት አመታት ያህል በፓርትሪያርክነት መንበር ላይ የተቀመጡት አቡነ ማትያስ በዙሪያቸው በከበቧቸው የሕወሃት አባላት በሆኑ ካህናት ግፊትና ተጽእኖ ከሌሎች አባቶች ጋር እየተጋጩ ከቤተክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ማህበራት ጋር እየተወዛገቡ መቀጠላቸው ሲነገር ቆይቷል። አሁንም ከቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና በቤተክርስቲያኒቱ ስር ከሚንቀሳቀሱ ማህበራት ጋር በፈጠሩት ውዝግብ ተግባብተው መስራት እንደተሳናቸው ተገልጿል። ከዚሁ ጋር በተያይዘ አቡነ ማትያስ ስልጣናቸውን ሊለቁ እንደሚችሉ በቃል መናገራቸውም ይፋ የሆነው በዚሁ ሳምንት መሆኑን የሀራ ተዋህዶ ዘገባ አመልክቷል። እንደዘገባው ከሆነ በቃል ያቀረቡትን መልቀቂያ በቅርቡ በጽሑፍ ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል። በቀጠዩ ሰኞ የሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም በአቡነ ማትያስ ቅሬታና ተቃውሞ ዙሪያ ይነጋገራል ተብሎ ይጠበቃል። የተለመደው የመንግስት ጣልቃ ገብነትም ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል። በቤተክርስቲያኒቱ ህግ መሰረት አንድ ፓትሪያርክ ስልጣኑን የሚያጣው ሀይማኖታዊ ስህተት ሲፈጽም አልያም ታማኝነቱንናን መንፈሳዊ አባትነቱ ተቀባይነትን ያጣ ከሆነና ይህም በተጨባጭ ተረጋግጦ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲወሰን እንደሆነ በሕገ ቤተክርስቲያን ተደንግጓል።ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ የአቡነ ጳውሎስ ሞትን ተከትሎ ስድስተኛው ፓትሪያርክ ናቸው። የኢትዮጵያ የአገዛዝ ስርዓት ቤተ-ክርስቲያኒቷን የፖለቲካ መናኸሪያ ባማድረጉና አቡነ ማትያስም እንደ አቡነ ጳውሎስ የፖለቲካው ቁማር በቀላሉ የማይረዱት በመሆኑ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ በየ ጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁሙ ነበር።

 

የፌደሬሽን ምክር ቤት በእነ ዶክተር መረራ ጉዲና ጉዳይ ላይ የተጠየቀውን  የህገ-መንግስት ትርጉም ምላሽ ሰጠ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የተጠቀሱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ስም ዝርዝር ለተከሳሾች ሊደርስ ይገባል፣ አይገባም በሚለው ክርክር ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት በጠየቀው መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ ምላሹን ሰጥቷል።የዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቆች ለተከሳሽ የምስክር ስም ዝርዝር እንዲሰጥ የሚፈቅደውን የህገ መንግስቱን አንቀፅ 20/4  በመጥቀስ የምስክር ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው ተቃውሞ ያቀረቡ ቢሆንም የፌደሬሽን ምክር ቤት የፀረ ሽብር አዋጁም ሆነ የምስክር ጥበቃ አዋጅ ከባድ ወንጀሎች ላይ የሚቀርቡ የምስክሮች ለደህንነታቸው ሲባል ስም ዝርዝር ባይሰጥ ህገ መንግስቱ ጋር የማይጋጩ በመሆኑ ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ትርጉም አያስፈልገውም የሚል መልስ ሰጥቷል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የእነ ዶ/ር መረራ ጉዳይ ከባድ ወንጀል መሆኑን በመግለፅ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይገለፅ ብይን ሰጥቶ የምስክሮች ቃል እንዲሰማ ለጥቅምት 24/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራ ጉዲና የእምነት ክደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በጠየቀው መሰረት ዶ/ር መረራ የተጠቀሰውን ወንጀል ” አልፈፀምኩም! ጥፋተኛም አይደለሁም!” ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። የዶ/ር መረራ ጠበቆች የፌደሬሽን ምክር ቤት ምላሽ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ይግባኝ እንደሚሉ ገልጸዋል።በዶክተር መረራ የክስ መዝገብ ዶክተር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ ጃዋር መሀመድ፣ኢሳትና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደሚገኙበት የሚታወቅ ሱሆን ከታሰሩ አስራ አንድ ወራት ሆኗቸዋል።በሀገር ውስጥ በሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ  ዶክተር መረራን ጨምሮ ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈቱ ህዝቡ እየጠየቀ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

ባለፈው ነሐሴ ወር በአዋሽ ሰባት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ551 ሺህ ዶላር በላይ ሲያሸሹ የተያዙ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

ባለፈው ነሐሴ ወር በአዋሽ ሰባት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ551 ሺህ ዶላር በላይ ሲያሸሹ ተገኙ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ። የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርብ እለት በዋለው ችሎት ገንዘቡን በህገ-ወጥ መንገድ ሲያስተላልፉ በተያዙት በአቶ ሀበኔ አረብኑር ላይ የስምንት ዓመታት እስራትና የ100 ሺሕ ብር ቅጣት ሲወስን፤ በአቶ ሐመድ መሐመድ ላይም ተመሳሳይ የስምንት ዓመታት ጽኑ እስራት እንደተበየነባቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በህገ-ወጥ መንገድ ሊያሸሹት ነበር የተባለው  551,771 ዶላርም በቅርቡ ከኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲውል ፍርድ ቤቱ ጨምሮ መወሰኑን መረጃው አመልክቷል። የሶማሊ ክልል መንግስት አካል ነው የተባለው አቶ ሀበኔ አረብኑር ባለፈው ነሐሴ ወር 551 ሺ 771 ዶላርና ብር ከአዲስ አባባ ወደ ሶማሌ ክልል ሲያጓጓዝ አዋሽ ሰባት አካባቢ ባለ የጉምሩክ ኬላ መያዙ የተዘገበ ሲሆን ገንዘቡ ምናልባትም የህወሓት ባለስልጣናትና የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ሳይሆን እንደማይቀር የተለያዩ ግምቶች ተሰጥተው ነበር።በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የምንዛሬ(ዶላር) እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደ ሲሆን በቅርቡም ዶላርን ጨምሮ በሌሎች የውጭ ሀገር ገንዘቦች ላይ የምንዛሬ ማሻሻያ መደረጉ የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል

የምንዛሪ መጠኑ ወደ 45 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የአሜሪካ ዶላር ወደ ውጭ ሊወጣ ሲል መያዙን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ አርብ ጥቅምት 8 /2010 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሀረር ባቢሌ መግቢያ ቶጎ ጫሌ ኬላ አካባቢ ድምሩ 1 ሚሊዮን 656 ሺ 264 የአሜሪካ ዶላር ወደ ውጭ ሊወጣ ሲል ተይዟል፡፡ዶላሩ ከሐረር ከተማ በሚኒባስ ሲጓጓዝ የነበረ ሲሆን፥ ከሃረር እስከ ቶጎ ጫሌ ድረስ በተለምዶ “ኮስትር”ተብሎ በሚጠራው ተሽከርካሪ ከተጓጓዘ በኋላ በህብረተሰቡ ጥቆማ ቶጎ ጫሌ ኬላ ላይ ለመያዝ እንደተቻለ ተገልጿል፡፡ ከዶላሩ በተጨማሪም 580 ሺህ የሳዑዲ ሪያል፣32 ሺ 750 የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ገንዘብና አንድ ሹህ 851 የኳታር ገንዘብ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር መያዙ ታውቋል።በዚህ መሰል ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በርካታ የሀገሪቱ አንጡራ ሀብት እንደተዘረፈ ይገመታል።የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ባለፍት  አስር ዓመታት ብቻ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈው ከሀገር  እንዳወጡት የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት አጋልጠዋል።

 

የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ የውሀ ሀብት ሚኒስትሮች ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ መምከራቸው ተገለጸ

የሦስቱ ሀገራት ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ የተጀመረውን የአባይ ግድብን ከጎበኙ በሗላ በአዲስ አበባ መምከራቸው ተገለጸ።ኢትዮጵያ እየገነባች ያለቸው የአባይ  ግብድ ግንባታ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ካለ በሚል ጥናት እንዲያደርጉ ለሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች መሰጠቱ የሚታወስ ሲሆን ባለፈው ሐሙስ እለት ከሚኒስትሮቹ ጋር መምከራቸው ታውቋል። በኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ እ.ኤ.አ 2015 የተመረጠው የጥናት ቡድኑ በአስራ አንድ ወራት ጨርሶ በጥር 2016 ጥናቱን እንዲያስረክብ ስምምነት የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በማራዘሙ ከዚህ መድረሱን የግብጽ የዜና ተቋማት እየገለጹ ነው።በተለይም ግብጽ ግድቡ ተጠናቆ የውሀ ሙሌት ሲጀመር ከ1000 ሜትር ኩብ  600 ሜትር ኩብ ይቀንስብኛል በማለቷ ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። አዲስ አበባ ላይ በነበራቸው የሦስትዮሽ ስብሰባ ላይ ግብጽ እ.ኤ.አ 1956 በቅኝ ገዥዎች የተደረገውን የውሀ አጠቃቀም ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቃ ኢትዮጵያ ውድቅ እንዳደረገችው ታውቋል።ግብጽ በግድቡ ግብታ በተያያዘ እንቅፋት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑንም ኢትዮጵያ እየከሰሰች ትገኛለች። የአባይ ግድብ በ2003ዓ.ም ተጀምሮ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሰባት አመቱ ገና 60 በመቶ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

 

 

 

 

 

 

Categories: Uncategorized

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s