ፖለቲካ

የጎሳ ፌደራሊዝሙ መጨረሻ ወዴት?አርሴማ መድህኑ

ህወሓት/ ኢህአዴግ ከ17 ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በሗላ የዳግማዊ ሚኒሊክ ቤተ-መንግስትን በ1983 ዓ.ም  በተቆጣጠረ በዓመቱ አዲስ አበቤዎች አንድ ለእናቱ እያሉ በሚጠሩት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከ30 ሺህ ሰዎች በላይ ጢም ባሉበት አንድ ወጣት ነብይ በሚያስብል መልኩ የሚከተሉትን ስንኞች ለታዳሚዎቹ አቀነቀነ።ስንኞች ከስድት መስመር ባይበልጡም በያዙት መልዕክት ግን ስታዲየሙ ባንድ እግሩ ቆሞ፤ በአንድ ድምፅ ይደገም–ይደገም ተባለ። ተጮኸ–  በቦታው የተገኙ ከሦስት የማይበልጡ የህወሓት ባለስልጣናት በህዝቡ ጩኸትና በዘፈኑ መልዕክት ተበሳጩ፤ አቋርጠውም ወጡ።በስቴዲየሙ የሞላው ህዝብ ግን አርቲስቱን ይደገም!–ይደገም! በማለት የብሶት ጩኸቱን ቀጠለ።  አርቲስቱም ደገመ!–እንዲህም አለ

በሶማሊያ ችግር አብረን ስንጨነቅ፤

በዩጎዝላቪያ ቆመን ስንሳለቅ፤

በእንጀራ አባታችን በሩሲያ ስንስቅ፤

ከእነሱ ሳንማር ካለፍነው በዋዛ፤

አርባ መንግስት ሆነን ክልል ስናበዛ፤

እንዳንጠያየቅ ፓስፖርትና ቪዛ።አለ።ታማኝ በየነ 1984 ዓ.ም አዲስ አበባ ስታዲየም።

አዎ የጥበብ ባለሙያው ከ26 ዓመታት በፊት ያስጠነቀቀን አሁን መራራ እውነት ሆኗል።ለምንስ እንዲህ እንዲሆን ተፈለገ? የትስ ያደርሰናል? በምንስ ከዚህ ክፉ በሽታ መላቀቅ ይቻላል የሚሉት ወቅታዊና አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው።እናም በዛሬው ጹሁቻችን የኢትዮጵያን የፌዴራል መንግስት አወቃቀር፣ በየ ጊዜው እየተፈጠሩና እያደጉ የመጡትን የእርስ በእርስ ግጭቶች መንስኤና ኤትዮጵያ አሁን ካለችበት አረንቋ በምን መንገድ ልትወጣ ትችላለች የሚሉትን በተቻለን መጠን ዘመራ ራዲዮ ሀሳቧን ታካፍላለች።

የኢትዮጵያ መንግስት አወቃቀርና ፌዴራሊዝሙ

እንደሚታወቀው የፌደራሊዝም የመንግስት አወቃቀር ጽንሰ-ሀሳቡ “ማዕከላዊ መንግስት” ለክልል ግዛቶች ስልጣኑን ማካፈል ነው። የፌዴራል መንግስቱ አካል የሆኑት ግዛቶች በተለያየ መልኩ ሊካለሉ ይችላሉ።ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ሀገራት ተግባራዊ የተደረገውና አበረታች ውጤት እያመጣ ያለው የማካለል ዘይቤ “መልክዓ-ምድራዊ ወይም ጂኦ-ግራፊያዊ ስልት ዋነኛው ነው። በዓለማችን የተሳካ የፌደራል ስርዓት የዘረጉ ሀገራት አሉ።ለአብነትም  አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመን፣ ሥዊዘርላንድ እና የመሳሰሉት ሀገራት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሀገራት ፌደራሊዝምን ተግብረው አንድነታቸውንና  ኢኮኖሚያቸውን አበልፅገዋል።በሰሜን  አሜሪካ ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ ከ52 በላይ ግዛቶች እራሳቸውን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ ጠላቶቻቸውን በጋራ  ለመመከት ከ200 ዓመታት በፊት ተሰባሰቡ። እግረ-መንገዳቸውንም  በፌደራል ስርት አወቃቀር አንድ ልዕለ- ሀያል ሀገረ-አሜሪካን መመስረት ቻሉ። ምንም እንኳ በሀገረ-አሜሪካ ከተለያዩ አህጉራት የተሰባሰቡ የተለያየ ሀይማኖት፣ቋንቋ፣ባህልና ስነ-ልቦና ያላቸው ቢሆኑም ከግለሰብ ማንነት ይልቅ ሁሉንም የሚያሰባስበው የአሜሪካዊ ማንነት ወይም አሜሪካን ናሽናሊዝም ይገዝፍባቸው ። ሌሎች ጅኦ ግራፊያዊ ፌዴራሊዝም የሚከተሉ ሀገራትም እንዲሁ።  የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ “ዘ አዳሲቲ ኦፍ ሆፕ-The Audacity of Hope” በተሰኘው መጽሀቸው ይህንን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ “ የጥቁር አሜሪካ፣ የነጭ አሜሪካ፣ የላቲኖ አሜሪካ ወይም የኤዥያ አሜሪካ የሚባል የለም። ያለው የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች ብቻ ነው።” በማለት ጽፈዋል። ይህንን ሀሳባቸውን ደጋግመው በመናገራቸውም ሴናተር ከነበሩበት የኤሊኖስ ግዛት  ወደ ነጩ ቤተ መንግስት  ለመግባት ረድቷቸዋል።  ይህ ሲባል ግን በፌደራል ስርዓት ውስጥ የባህልና የቋንቋ ጥያቄዎች አይነሱም ማለት አይደለም። ሆኖም ሀገርን ለመበታተን ሳያመቻቹ ጥያቄውን በጥንቃቄ ያስተናግዱታል። የካናዳው የኩቤክ አስተዳደር ለዚህ ምሳሌ መሆን ይችላል። ከ150 አመት ገደማ በፊት ወደ ካናዳ በኮንፈደሬሽን የተቀላቀለችው የኩቤክ ግዛት በካናዳ ፌደራሊዝም ውስጥ ጥያቄዋ በልዩ ሁኔታ ይታያል። ፌደራሊዝም በተገቢው መንገድ ስራ ላይ ከዋለ  ሀገር እንዳይበተን አሰባስቦ ለመያዝ ዋነኛ አመራጭ ሀሳብ እንደሆነ የዘርፉ ጠበብቶች ይመክራሉ።

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ የኢህአዴግ የፓርቲ አመለካከት የተጠናወተው ነው በማለት የሚተቸው በ1987 ዓ.ም የጸደቀው ህገ-መንግስት በአንቀፅ 46 ላይ የፌዴራል መንግስት በክልሎች የተዋቀረ ነው ይላል። ክልሎች የሚዋቀሩትም በህዝብ አሰፋፈር፣ቋንቋ፣ማንነትና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ዝቅ ብሎ በአንቀጽ 46/1 ላይ ተቀምጧል። በ9 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳድር የተዋቀረው የኢትዮጵያ የጎሳ የፌዴራል ስርዓት በብዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዘንድ ተቀባይነት የለውም።ለዚህም የአማራ ተወላጆች ክልሎች ሲዋቀሩ ሆን ተብሎ አማራን ለመጉዳት ነው በማለት የክልሎችን አከላለል እንደማይቀበሉት በተለያየ አጋጣሚ ያጸባርቃሉ። በጎንደር ወልቃይት፣ በጎጃም መተከልና በወሎ ራያ ወደ ሌላ ክልል መካለላቸው በአማራው ላይ የተሰራ ሴራ ነው ይላሉ።በወቅቱ ክልሎችን በበከለል ረገድ ከህወሓት ቀጥሎ ፊት አውራሪ የነበረው የኦነግ ምክትል ጸሀፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ በቅርቡ ለጀርመን ድምጽ በሰጡት ቃል “ክልሎችን ስናዋቅር ደርግ ቋንቋን መሰረት አድርጎ ያስጠናው መረጃ” ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ቢሉም በብዙዎች ዘንድ ውሃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኙትም።

 

በየ ጊዜው እየተፈጠሩና እያደጉ የመጡት ግጭቶች መንስኤ

በኢትዮጵያ የህዝብን እሴቶች የጠበቀና ከዘመኑ ጋር መሄድ የሚያስችል ስርዓተ-መንግስት ኣለመኖር እንደመሰረታዊ ችግር ይታያል።በተለይም ከወታደራው ደርግ ጀምሮ የህዝቡን መብት የሚያከብር ስርዓት ሀገራችን አላገኘችም።በዚህም  ሰላም፣ እኩልነት፣ ኣንድነትና ብልፅግና፣ የፖለቲካዊ ባህላችንና በአለም አቀፍ መድረክ ያለን ተቀባይነት እየራቀን ሄዷል። ባለፉት 26 ዓመታት በትረ-ስልጣኑን የተቆናጠጠው የህወሓት/ ኢህአዴግ  የአገዛዝ ስርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ ጠላትና ወዳጅ ህዝብ በማበጀት አንዱን ለሌላው ጠላት አድርጎ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት  የሀገርን አንድነት በማናጋት ይኸው የውድቀቱ ጫፍ ላይ የደረ  ይመስላል። ስርዓቱ ዘርን፣ አካባቢንና የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት በማድረግ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሲያደርግ፤  የስርዓቱን ቁንጮ ባለስልጣናትን ዘርና የፖለቲካ አመለካከት ያልመሰሉ ብዙሃኑን የኢትዮጵያን ወጣቶች በሀገራቸው ባይተዋር ሆነው ቀጥለዋል።ሀሳቡ ጠቅለል ሲደረግ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል በሀገሪቱ ውስጥ ባለመኖሩና ጎሳን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም  ባለፉት 26 ዓመታት በሀገሪቱ ተግባራዊ መሆኑ ለማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት ሀገሪቱን እየዳረጋት ይገኛል። ይኸው የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ገቢር ከተደረገ ጀምሮ በአማራና ትግራይ፤ በአማራና አፋር፣በትግራይና አፋር፣ በኦሮሚያና ሶማሌ፤ በኦሮሞና ሲዳማ፣በኦሮሞና ጋምቤላ፣በኦሮሞና ቤንሻንጉል ጉምዝ፣በኦሮሚያና አፋር ወዘተ በርካታ የሰው ህይወት የጠፋባቸው ግጭቶች ተካሂደዋል።ከነዚህም ውስጥ የአማራና ትግራይ ክልሎች በወልቃይት ጠገዴ እጅግ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን አካሂደዋል።አሁንም ቀጥሏል።በአካባቢው የሚኖሩ አብዛኛዎቹ  የወልቃይት አማሮች ሀገር ጥለው ተሰደዋል። ሌላው በቅርቡ አነጋጋሪና አሳሳቢ የሆነው የኦሚያና የሶማሌ ክልሎች የእርስ በእርስ ግጭት ነው።

ቁጥራቸው ከ200 እስከ 300 የሚገመት ሰዎች የሞቱበትና በጥቅሉ 2500 ሺህ ሰዎች በላይ የተፈናቀሉበት የኦሮሞና የሶማሌ ጎሳዎች ግጭት እንደ ወልቃይት ጠገዴው ሁሉ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ጊዜ አስቆጥሯል።ቀደም ሲል እንደገለጽነው ህወሓቶችና ኦነጎች ስልጣን ከተቆጣጠሩ በሗላ ሀገሪቱን በጎሳ ሲከፋፍሉ ኦሮሚያና ሶማሌ ከድሬ ደዋ ወደ ደቡብ የሀገሪቱ አቅጣጫ በመዝለቅ ሞያሌ ድረስ ይዋሰናሉ።በሁለቱ ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚገኙ 420 ቀበሌዎች የይገባኛል ጥያቄ በክልሎቹ ተነሳ።ጉዳዩን እልባት ለመስጠት በማለት በ1997 ዓ.ም ህዝበ-ውሳኔ እንዲያካሂዱ ተደረገ።340 ቀበሌዎች ወደ ኦሮሚያ መጠቃለልን ሲመርጡ፤80 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሶማሌ ክልል አስተዳድር ለመጠቃለል ውሳኔ ማሳለፈቸውን ይነገራል።ይሁን እንጂ እንደተባለው የህዝቡን ውሳኔ ተከትሎ ክፍፍሉ ላይ ሁለቱ ክልሎች መግባባት እንደተሳናቸውም ቀጥሏል። የሶማሌ ክልል በእኛ በኩል የነበሩትንና ወደ ኦሮሚያ መካተትን የመረጡ ቀበሌዎችን በወቅቱ ብናስረክብም፤ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ ይህን አላደረገም በማለት የሶማሌ ክልል ይከሳል።የኦሮሚያ ክልል አስተዳድር በበኩሉ ይህንን ክስ አይቀበልም። እንዲያውም የክልሉ የኮምንኬሽን ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ ለቪ ኦ ኤ በቅርቡ ሲናገሩ “ከባለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ ከሶማሌ ክልል የሚነሱ የታጠቁ ሀይሎች ወደ ኦሮሚያ ግዛት እየገቡ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።ታጣቂዎቹ ጥቃት ሲፈፅሙ የአካባቢ ነዋሪዎች በሚሸሹበት ጊዜ የሶማሌ ክልል ሰንደቅ አላማን በመስቀል አካባቢውን የሶማሌ ክልል አካል ለማድረግ እየሰሩ ነው” በማለት ተናግረዋል።የሶማሌ ክልል በበኩሉ የኦሮሚያ ክልል የመሬት ወረራ ፈፅሞብኛል፤የፌዴራል ስርዓቱንም ለማፍረስ እየሰራ ነው ሲል ይደመጣል።  የሶማሌ ክልል በየጊዜው የሚያወጣው መግለጫና እንደፈለገ ንጹሀን ዜጎችን ሲያፈናቅል ላየ በአንድ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ያለ ሳይሆን አንድ ሌላ ሉዓላዊ ሀገር ነው የሚመስለው። ብዙዎች የህወሓት ባለስልጣናት ከሶማሌ ክልል ጎን እንዳሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።አንዳንዶችም ሶማሊያ እስከ ባሌ ድረስ ለመውሰድ በ1970 ዓ.ም ሞክራ ያልተሳካላትን አሁን በአብዲ መሀመድ በኩል እጇን አስገብታ ሊሆንም ይችላል የሚሉም አልጠፉም።ያም ሆነ ይህ ግን የዜጎች ህይወት እያጠፋና በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብታቸውን እየገደበ በመሆኑ ሳይቃጠል በቅጠል እንሚባለው ቢደረግ መልካም ነው እንላለን።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አረንቋ በምን መንገድ ትውጣ?

በእርግጥ ሀጋራችን ከገባችበት ውስብስብ ችግር የመውጫ መፍትሔ ሀሳብ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣የሲቪል በማህበራትና ሙህራን በየጊዜው ከመለገስ ተቆጥበው አያውቁም።አሁን በግፍ  እስር ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ሳይንስ ሙህሩ ዶክተር መረራ ጉዱና የኢትዮዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች” በሚለው መጽሀፋቸው እንደ መፍትሄ ሀሳብ ያስቀመጡት የመፍትሄ ሀሳብ ሰሚ ጆሮ ቢያገኝ ህዝባዊ እንቅስቃሴው ጫፍ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ ምናልባትም ሀገሪቱ ወደ እምትፈልገው የነፃነት ጎዳና ሊያደርሳት ይችላል።

ዶክተር መረራ ከላይ በጠቀስኩት መጽሀፋቸው  የአማራና የኦሮሞ ሊህቃን የፖለቲካ መስመር የለውጡ ማነቆ እንደሆነ በገፅ 263  ላይ እንዲህ ይላሉ። “ በተቃዋሚው ጎራ ብዙ ሳይቀሳቀስ እያየሁ ያለሁት የኦሮሞና የአማራ ሊህቃን ፖለቲካ ነው።የሁለቱም ሊህቃን ፖለቲካ በዋናነት በሁለት ጫፎች ላይ ቆሞ ገመድ ከመጎተት ወደ መሀል መጥቶ የጋራ ዲሞክራቲክ አጀንዳ መቅረፅ አልተቻላቸውም።ብዙዎቹ ሂሳብ የማወራረድ ፖለቲካን የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት ብቻ ሳይሆን የዛሬ 130 እና 140 ዓመታት በፊት የነበረውንም ጭምር የታሪክ ሂሳብ እንተሳሰብ የሚሉ ይመስሉኛል።የኦሮሞ ሊህቃናን ዋናው ችግራቸው የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ለመቅረጽ ከመጣር ይልቅ ለብቻቸው የሚደረገው ትግል የመንግስተ-ሰማያት አስተማማን መንገድ አድርገው ማምለካቸው ነው።” ይላሉ። በእርግጥም የትግራይ  ህዝብ ነፃ አውጭ  ቡድን ህወሓት አንዱ ከሌላው ጋር እንዳይተማመንና እንዳይተባበር ፖሊሲ አውጥቶ ከሦስት አስርት   ዓመታት በላይ ሰርቶበታል።በተለይም የሀገቱን የፖለቲካ ስርዓት መወሰን የሚችለውን የአማራና የኦሮሞን ህዝብ በመካከሉ ያለውን ቁርሾ በማባባስ እንዲሁም ሌላም የፈጠራ ታሪክ በመንዛት ተጋብተውና ጠላትን በጋራ መክተው ለዘመናት አብረው የኖሩትን ሁለቱን ጎሳዎች ወይም ብሄሮች አብረው እንዳይቆሙና የወደፊት እድላቸውን በጋራ እንዳይወስኑ ለማድረግ ብዙ ጥሯል።ይህን ሁሉ የፕሮጋንዳ መዓት አልፈውም ሲተባበሩና አንዱ ለሌላው አለውልህ ሲለው ይስተዋላል።ለምሳሌም አምና በጎንድር ፣በአዳማ፣ አሁን ደግሞ በወሊሶ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲደረጉ የሁለቱን ማህበረሰቦች ትስስርና አጋርነት ያንፀባርቃሉ።ከትናንት በስቲያ አርብ እለት ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ከ200 በላይ የሚልቁ ወጣቶች ጣና የእኛም ነው በማለት ያሳዩት የትብብር መንፈስ ሌላው ማሳያ ነው።በእርግጥ እስካሁንም ቢሆን ህዝቡ ጋር የጎላ ችግር እንደሌለ የሚታወቅ ነው።ችግሩ የፖለቲካ መሪዎችና ከአንዳንድ ሙህራን ጋር ነው።

እናም ሀገራችን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ለመውጣት አሁን በህዝቡ  የተፈጠረውን የመተባበር ስሜት፤ የሁሉም ወገኖች ሊህቃን አጀንዳ በመቅረጽና መንገድ በመምራት ረገድ ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ በማቅረብ የዛሬው ጡመራችንን እዚህ ላይ እናብቃ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላም ትኑር!

መልካም ሳምንት!

 

 

 

Categories: ፖለቲካ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s