ዜና

Zemera Radio Weekly News 16 Oct,2017

 

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቬዥን እና ራዲዮ ኢሳት የተመሰረተበትን ሰባተኛ አመት በኖርዌ ኦስሎ አከበረ

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግድያና እስራት ቀጥሏል

የህወሓት አገዛዝ ወታደሮች በተለያዩ የኦሮሚያ  አካባቢዎች ግድያና እስራት እየፈጸሙ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ አርብ ዕለት በቦረና ዞን በቡኬ ከተማ ስድስት ሰዎች መገደላቸው የታወቀ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ በሻሸመኔ አራት ሰዎች በመከላከያ ወታደሮች መገደላቸው ታውቋል፡፡ በህዝብ ላይ ጦርነት ያወጀው የህወሓት ስርዓት፣ ለሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ዜጎች ላይ የጥይት ናዳ ማዝነቡን ቀጥሎበታል፡፡ በቦረና ዞን ግድያ የተፈጸመው ህብረተሰቡ የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ ወደ ሶማሌ ክልል ሲጓዙ የነበሩ የመከላከያ መኪኖችን አናሳልፍም በማለቱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡በዚህም የተነሳ የአካባቢው ህብረተሰብ የጦር መሳሪያ የጫነውን መኪና አላሳልፍ ብሎ መንገድ በመዝጋቱ፣ በስፍራው የነበረው የህወሓት ሰራዊት ስድስት ሰዎችን በመግደልና 18 ሰዎችን በማቁሰል ተቃውሞውን በትኖታል፡፡መኪኖቹ በአሮሚያ መንግስት የታገቱ ሲሆን የህወሓት ጄኔራሎች ከኦሮሚያ የጸጥታ አባላት ጋር የታገቱትን የጦር መሳሪያ የጫኑ መኪኖችን ለማስለቀቅ ድርድር እያካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ወጥተዋል።ህዝባዊ ተቃውሞው በአምቦ፣ወሊሶ፣አዳባ፣ጊንጪ፣መቱና በሌሎች ከተሞችም ባለፍት አራት ቀናት ተካሂዷል። የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወገኖቻችንን አይግደል፤ ድንበራችን ይከበር፤ አባይ ጸሐዬ ሌባ ነው! የሚሉና ሌሎች መፈክሮች በተንጸባረቁበት ሰልፎች ላይ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ እንዲሁም በርካቶችም ለእስር ተዳርገዋል ሲሉ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

በአማራና ቅማንት ማህበረሰብ መካከል የተደረገው የህዝበ-ውሳኔ ውጤት ሐሙስ እለት ይፋ  ተደረገ

እራሱን የ“ፌዴሬሽን ምክር ቤት” በማለት የሚጠራው የህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚ ተቋም ለዘመናት በመከባበር አብሮ የኖረውን የአማራና የቅማንት ማህበረሰብን  ለመነጣጠልና ለመከፋፈል ብአዴንና ህወሓት ሲሰሩ ቆይተዋል።በመሆኑም 42 ቀበሌዎችን ያለ ህዝብ ፍላጎት “የቅማንት አስተዳድር” በማለት ሲያካልል በ8 ቀበሌዎች ደግሞ ህዝበ-ውሳኔ መስከረም 7/2010 ዓ.ም ማድረጉ ይታወሳል። 7ቱ ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳድር መሆንን ሲመርጡ፤ በቆላ ድባ ወረዳ ስር የምትገኘው ሎምየ የተባለች ቀበሌ  አዲሱን የቅማንት አስተዳድርን  መቀላቀል እንደመረጠች በወቅቱ ተገልጿል። ይሁን እንጂ በሎምየ ቀበሌ የተካሄደው ህዝበ-ውሳኔ እድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሰና ያልታወቁ መራጮች በመሳተፋቸው ምክንያት ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉም ተዘግቧል። ህወሓት ከጀርባ በመሆን ይመረዋል ተብሎ የሚታመነውን የሁለቱን ማህበረሰብ የመከፋፈል አጀንዳ ከፍተኛ ተቃውሞ አሁንም ድረስ እየቀረበበት ይገኛል። ምርጫ ቦርድ የህዝበ- ውሳኔውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በላከለት መሰረት “ሰባቱ ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳደር እንዲቀጥሉ፤ አንዱ ቀበሌ ደግሞ በአዲሱ  የቅማንት አስተዳደር እንዲጠቃለል” በማለት ምክር ቤቱ መወሰኑን የደረሰን መረጃ ጠቁሟል።ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የኢህአዴግ ህገ-መንግስት በክልሎች ወይም በሁለት ግዛቶች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች  መፍትሄ የመፈለግ ሀላፊነት የተሰጠው ቢሆንም የሚፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም።በአማራና ትግራይ መካከል፣በትግራይና አፋር ፣በኦሚያና ጋምቤላ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ፣እንዲሁም በቅርቡ ከ200 ሰዎች በላይ የሞቱበትና ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉበት የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች  ግጭት ተጠቃሽ ነው።

 የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ እንዳስታወቀው  ጥቅምት 1/ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የብር የመግዛት አቅም በ15 ፐርሰን  እንደሚቀንስ አስታውቋል። በዚህም መሰረት አንድ ዶላር አሁን ካለበት የ23.54 ብር ምንዛሬ  ላይ የ3.5 ብር ጭማሪ በማሳየት ወደ 27.04 ብር ይሆናል ተብሏል። ኤይ ኤም ኤፍ..የኢትዮጵያ መንግስት የብርን የመግዛት አቅም ማሻሻያ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ሀሳብ ሲያቀርብ በመቆየቱ፤ አሁን የተደረገው ማሻሻያ ለአይ.ኤም.ኤፍ. ምላሽ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል። የአንድ ሀገር ገንዘብ የመግዛት አቅም የሚቀንሰው (Devaluation) ወደ ውጭ የሚላኩ እቃዎች(Export) እና ወደ ሀገር የሚገቡ የሸቀጥ እቃዎች(Import) አለመመጣጠን ሲኖር እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው በዋናነት ቡና፣ ቆዳና ሌጦ ናቸው።በምትኩ የግብርና መሳሪያዎችን፣የአውቶ ሞቲብ መለዋወጫዎችን፣የግንባታ መሳሪያዎችን፣አልባሳትንና የመሳሰሉትን እቃዎች ወደ ሀገር ታስገባለች።እ.ኤ.አ በ2014 አንድ ጥናት እንደጠቆመው  ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ለሚገዙ  ለእቃዎች ግዥ ወጭ ታደርጋለች። ኤክፖርት የምታደርገው የሸቀጥ እቃ የግዥዋን ከ7 ፐርሰንት በላይ እንደማይሸፍንም ጥናቱ ያሳያል።

ማሻሻያውን ተከትሎ ሀገሪቱ ከአለም ባንክና ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት ያለባት  ከፍተኛ <እዳ> በ15 ፐርሰንት እንደሚጨምር ታውቋል። እንዲሁም በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ግሽበትን ሊያስከትል እንደሚችልም ባለሙያዎች አስታውቀዋል።የህወሓት የአገዛዝ ቡድን በ1983 ዓ.ም በትረ-ስልጣኑን ሲቆጣጠር አንድ የአሜሪካን ዶላር በ2 ብር ይመነዘር እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በየ አስር ዓመቱ የሚደረገው  የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘሙ ተጠቆመ

በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው አራተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባልታወቀ ምክንያት ተራዘመ፡፡ለቆጠራው አስፈላጊ የሆኑ የሎጂስቲክ ግብዓቶችና አቅርቦቶች በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ቆጠራው መራዘሙ  ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለቆጠራው ያስፈልጋሉ ተብለው የተገዙ 180 ሺሕ ዲጅታል ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 126 ሺሕ ፓወር ባንኮች ግዥ መደነቃቀፎች ገጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አብዛኛዎቹ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል፡፡ የግዥ መጓተት ለቆጠራው መራዘም ምክንያት ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ 665 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው ዕቃዎች ግን ባለፈው ሳምንት በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ለዘንድሮው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ 3.1 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት ታውቋል። በኢህአዴግ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 103 መሠረት የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ መደረግ እንዳለበት ቢደነግግም ላልተወሰ ጊዜ መራዘመኑን ሪፖርተር ዘግቧል።ቆጠራው መራዘሙ የህገ መንግስት ጥሰት እንዳስከተለም ባለሙያዎች አስተያየት እየሰጡ ነው። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የቆጠራውን መራዘም ያረጋገጡ ሲሆን የተራዘመበትን ምክንያት መንግስት በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። እንደ አስተያየት ሰጭዎች ከሆነ ግን ቆጠራው የተራዘመበት ዋና ምክንያት አሁን በሀገሪቱ ላይ የተከሰተው “ህዝባዊ አመጽ” እንደሆነ ይነገራልአ

እንቁጣጣሽ”  በሚ ለው ሙዚቃዋ  የምትታወቀው ድምፃዊት ዘሪቱ ጌታሁን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች ተባለ

  ድምፃዊት ዘሪቱ ጌታሁን ባደረባት ህመም ምክንያት በለገሀር ጠቅላላ ሆስፒታል በህክምና ስትረዳ ቆይታ ማክሰኞ እለት ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ላይ ህይወቷ ማለፉ ታውቋል። ድምፃዊት ዘሪቱ ጌታሁን በ1940ዎቹ አካባቢ በወሎ ክፍለ ሀገር “ኩታ በር” በተባለ አካባቢ እንደተወለደች የህይወት ታሪኳ ያስረዳል። አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “እንቁጣጣሽ”  የሚለው ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ስራዋ ሁሌም እንደ አዲስ የሚደመጥላት አርቲስት ዘሪቱ ጌታሁን ከ50 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት የበኩሏን በጎ አስተዋፅዖ አድርጋለች። እንቁጣጣሽ ከሚለው ተወዳጅ ስራዋ  በተጨማሪም ትዝታ በፖስታ፣የጥበብ አበባ፣እቴ ያገሬ ልጅና በሌሎች የሙዚቃ ስራዎቿ ትታወቃለች። ለቀናት በፊትም አጋፋው አርቲስት ሀብተሚካኤል ደምሴ በደረሰበት ከባድ የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት በሞት መለየቱ የሚታወቅ ነው።

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s