ዜና

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች  መካከል የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች  መካከል በድንበር ይገባኛል ጥያቄ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ከ55 ሺህ በላይ ህዝብ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለዋል ተባለ። የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ  የፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ባወጡት መግለጫ  ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች በሐረር፣ ጭናክሰን፣ ሚኤሶን፤በ ባቢሌ እና ድሬደዋ  ከተሞች በጊዜያዊነት በድንኳን ተጠልለዉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።አቶ አዲሱ አረጋ እንደገለጹት  ግጭቱ ከተከሰተበት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ከ400 ሺህ ሰዎች በላይ መፈናቀላቸውን ጠቅሰዋል።ግጭቱ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደ አዲስ አገርሽቶ ከመቶ በላይ ሰዎች እንደሞቱ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። በቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በቦረና፣በጉጂና በባሌ ግጭቱ የበረታባቸው አካባቢዎች ናቸው።በትናትናው እለትም ከድሬ ደዋ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ  ሀማሬሳ በተባለ ቦታ ከፍተኛ ጦርነት እንደተካሄደ ታውቋል። የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ፖሊስ እየተባለ የሚታወቀው የታጠቀ ሀይል በግጭቱ ውስጥ መሪ ተዋናይ እነደሆነ ይነገራል። በሌላ በኩል ማክሰኞ እለት የአወዳይ ከተማ ነዋሪዎች  በግፍ የተገደሉትን 28 የሶማሌ ጎሳዎች በጅጅጋ ከተማ አርብ እለት ስርዓተ-ቀብራቸውን አስፈጽመዋል።የሶማሌ ክልልም ለአንድ ሳምንት የሀዘን ቀን አውጇል።የፌዴራል መንግስት የሚባለው አካል ግጭቱን ለማስቆም እስከ ትናንት ቅዳሜ ድረስ የወሰደው እርምጃ አለመኖሩ ብዙዎችን አስደንግጧል።የሁለቱ ክልል መሪዎችም የሰው ህይወት እያጠፋ ያለውን ግጭት ከማስቆም ይልቅ ወደ ቃላት ጦርነት በመግባት እንዳባባሱት በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።ሀገሪቱ የምትከተለውን የጎሳ አወቃቀር በቶሎ ካላረመች ከዚህም የባሰ ይመጣል በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

**********

በዛሬው እለት በሚካሄደው የአማራና የቅማንት የማንነት ህዝበ-ውሳኔ ከፍተኛ ተቃውሞን እያስነሳ ነው

በዛሬው እለት በሚካሄደው የአማራና የቅማንት የማንነት ህዝበ-ውሳኔ ከፍተኛ ተቃውሞ እያስነሳ መሆኑ ታውቋል። ህዝበ ውሳኔው በአስራ ሁለት ቀበሌዎች ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በ4 ቀበሌዎች ድምጽ ለመስጠት የተመዘገ ሰው  አለመኖሩ ታውቋል።በዚህም ምክንያት ህዝበ-ውሳኔው በ8 ቀበሌዎች ብቻ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን በባህል፣በቋንቋና በሐይማኖት የተሳሰረ ቅማንትን ከአማራ ለመለየት የታሰበው በአካባቢው ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ይዞታ ለማዳከም ነው በማለት በጽኑ ይቃወማሉ።ሰሜን ጎንደር ወልቃይት ጠገዴን ህወሓት ካለፈው 26 ዓመታት ወዲህ ወደ ትግራይ መከለሉን በመቃወም መራራ ትግል እያደረግች ትገኛለች።

*******

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ የሚጠራው የቆሻሻ ክምር በድጋሜ ተንዶ የሰው ህይወት አጠፋ

 በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆሼ  እየተባለ በሚጠራው ቦታ የተከመረ የቆሻሻ ተራራ ለሁለተኛ ጊዜ ተደርምሶ የሰው ህይወት አጠፋ።ሐሙስ እለት በድጋሜ በተደረመሰው የቆሻሻ ክምር የስድስት ልጆች አባት የሆነ አንድ ግለሰብ መሞቱ ታውቋል።በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ቆሻሻው ሲደረመስ ሁለት ሰዎች በአካባቢው እንደነበሩና አንደኛው መሞቱን ገልጸው ስለ ሁለተኛው ሰው ማወቅ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።34 ሄክታር ስፋት እንዳለው የሚነገርለት ቆሼ ከ57 ዐመታት በላይ አገልግሎት ሰጥቷል። ባለፈው መጋቢት ወር የቆሻሻው ክምር በዙሪያው ባሉ ቤቶች ላይ ተንዶ ከ115 ሰዎች በላይ እንደሞቱና በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ቤት አልባ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።

*******

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የአደረጃጀት ማሻሻያ ሊደረግበት ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የአደረጃጀት ለውጥ ሊደረግበት እንደሆነ ገለጹ። አዲሱ  የአረጃጀት ለውጥም የክልሎችን አወቃቀር መሰረት ያደረገ እንደሚሆን  ባለስልጣናቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአራት ዓመታት በፊት ሲቋቋም ማኔጅመንቱ ለህንድ ኩባንያ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የተሻለ ውጤት አለማምጣቱ በሌላ አዲስ አደረጃጀት እንዲተካ ምክኒያት መሆኑ ታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገር ደረጃ 15 ዲስትሪክቶች ቢኖሩትም ሰባቱ በአንድ ክልል ውስጥ ናቸው። ይህም ለሁሉም ክልሎች በፍትሃዊነት እንደማይሰራጭ አመላካች ነው ተብሏል። በየክልሎቹ አዲስ የሚዋቀረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠሪነቱም ለክልሎች እንደሚሆን ተጠቁሟል።በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት በአዲስ አበባ ለንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እንቅፋት እንደሆነበት የአዲስ አባባ የንጹህ ውሀ መጠጥ አቅርቦት ባለስልጣን ሲያማርር ቆይቷል። ኢትዮ-ቴሌኮምም በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ጥራት ያለው አገልግሎት ለደበኞቼ እንዳላቀርብ አድርጎኛል በማለት ስሞታ ማሰማቱ የሚታወስ ነው። የአማራ ክልል መንግስትም ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በደል እየደረሰብኝ ነው በማለት ቅሬታውን  ማሰማቱ ይታወቃል። በአማራ ክልል ያሉ የኃይል ማስተላለፊያዎችና ትራንስፎርመሮች በደርግ ዘመን የተገነቡና ያረጁ በመሆናቸው ዘመኑ የሚጠይቀውን የ“ሀይል” አቅርቦት ለህዝብ ለማዳረስ አልቻልኩም በማለት አማሯል። ከ197 በላይ የሚሆኑ ፋብሪካዎች ግንባታቸውን ጨርሰው የሀይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው ብቻ  ወደ ሥራ አለመግባታቸውን የክልሉ  መንግስት ሲገልጽ ቆይቷል።

*******

ሳዑዲ አረቢያ የምህረት አዋጁን ለሦስተኛ ጊዜ አራዘመች

 የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በሀገሩ የሚኖሩ   ህጋዊ ፍቃድ  የሌላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ሳውዲን ለቀው እንዲወጡ ያወጣውን የምህረት አዋጅ ለሦስተኛ ጊዜ አራዘመ። ኪዘህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት የተራዘመው ይኸው አዋጅ አሁንም ከመስከረም 6/ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር መራዘሙን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።በሳውዲ አረቢያ ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ያለ ህጋዊ ፈቃድ የሚኖሩ ሲሆን ባለፈው መጋቢት የምህረት አዋጁን ተከትሎ 45 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የተለያዩ ተቋማት ገልጸዋል።ቀሪዎቹ  የሀገራቸውን አምባገነን አገዛዝ በመፍራት ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደማይፈልጉ ይገልፃሉ።ባለፈው ነሐሴ ወር ሳውዲ አረቢያ የወጣውን የምህረት አዋጅ ባለመጠቀም ወደየ ሀገራቸው ያልተመለሱ የውጭ ሀገር ዜጎችን በግዳጅ ለማስወጣት መዘጋጀቷን ገልፃ ነበር። በዚህም ሂዩማን ራይት ዎች ሳውዲ አረቢያን በመቃወም፤ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በሀይል ወደ ሀገራቸው እንዳትመልስ መማጸኑ የሚታወቅ ነው። ሳውዲ አረቢያ የአለም አቀፉ የስደተኞች የሰምምነት ህግ አባል ባለመሆኗ በሀገሯ ላሉ ስደተኞች ችግሩን እጥፍ ድርብ እንዳደረገባቸው ይነገራል

***********

በኬንያ መዲና ናይሮቢ 67 ኢትዮጵያዊያን መታሰራቸው ተሰማ

የኬንያ ፖሊስ ያለ ህጋዊ ሰነድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ 67 ኢትዮጵያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ዕሮቡ እለት ዥንዋ ዘገበ።ባለፈው እሁድ ናይሮቢ  የደረሱት፤ በከተማዋ ምስራቃዊ ከፍል ካዮሌ በተባለ ሰፈር በአንድ ቤት ውስጥ ታጭቀው መያዛቸው ተጠቅሷል።ኢትዮጵያዊያኑ ለፖሊስ እንደገለጹት  ኬንያ የመጡት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ነው ብለዋል። እስረኞቹ  ሐሙስ እለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።ከተከሳሾች መካከልም 40 የሚሆኑትን በአንድ ወር እስራትና እያንዳንዳቸው 20  ሺህ የኬንያ ሽልንግ ከፍለው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ  ውሳኔ አሳልፏል።27ቱ ተከሳሾች በበኩላቸው ወደ ኬንያ የገባነው በህጋዊ መንገድ በመሆኑ በነጻ ልንለቀቅ ይገባል በማለታቸው ጉዳዩን ለማጣራት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ቦታ 13 ኢትዮጵያዊያን ተይዘው ፍ/ቤት መቅረባቸውም ይታወቃል።ስደተኞች ላይ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለህገ-ወጥ ስደት መባባስ ድህነትና የመንግስታቱ የመብት እረገጣ  ዋና ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።

 

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s