ሬዲዮ ዘመራ

ሁሌ እናስታውሳቸው  ተቀብሮ እንዳይቀር አኩሪ ታሪካቸው!!

21764752_1652071648167319_1601505344250999775_n

ከመኮንን ተሰፋዪ

ጸጋዬ ወይን ገ/መድህን (ደብተራው) ማን ነው ???

በ አፓርታይድና ዘረኝነት ላይ የተመሰረተውን ኢሰብአዊና ዝቃጭ ኋላ ቀር ስርአትን የሚያራምደው ወያኔ ዶሮ ሳይጮህ ምንነቱን አውቆ የተዋጋውን ኢህአፓን በትረ-መንግስት ከመጨበጡም በፊት ቢሆን በዋና ጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት መነሳቱ ፀሃይ የሞቀ ገሃድ ሃቅ ነው።

በኢህአፓና በወያኔ መካከል የነበረው አሁንም ያለው መሰረታዊ ቅራኔ በኢትዮጵያዊነትና በትግራይ ዘረኝነት መካከል ያለ ቅራኔ ነው። ይሄም የሚፈታው በህዝባዊ አመፅ ብቻ እንጂ በድርድር አለመሆኑን ኢህአፓ በተለያየ ታሪካዊ ወቅቶች ለህዝብ ሲያስተምርና ሲያሳውቅ መቆየቱ ያደባባይ ሚስጥር ነው። ተሳስተውም ሆነ አውቀው ከወያኔ ጋር ሲሞዳሞዱና ለመመዳሞድ ሲቃጡ ተዉ ወያኔን ማመን ቀብሮ ነው እያለም ከመናገርና ከማሳሰብ ተቆጥቦ ያወቀበት ጊዜ የለም።

ፋሺስቱ ደርግ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” እያለ አገሪቱን በወጣት ኢህአፓዎች በደም ጎርፍ አጥለቅለቆ ከፈረጠጠ በኋላ ያ ቁስል ሳይደርቅ ዘረኛው ወያኔ የደርግ ስራ አስፈጻሚ በመሆን ግድያውንና ጭፍጨፋውን አፈናውንና እስራቱን በእጥፍ ድርብ ቀጠለበት። ደርግ በጭፍጨፋ አስተካከለለት ወያኔም አገር ማስገንጠሉን፤ አገር መሸንሸኑን፤ አገር መሸጡን ቀጠለበት!!!!

ጀግና የኢህአፓ ታጋዮችንም ድምጽ በሌለው መሳርያ ገድሎ ማጥፋት፤ አስሮ ደብዛ ማጥፋት ሥራዬ ብሎ ተያያዘው። ዋና ጠላቶቹን ያቃልና!!!!! ወያኔ ሆያ ሆዬ ጨፋሪዎችንና በአላማቸው በጽናት ቆመው የሚታገሉትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለሆነ ኢህአፓን በምንም አይነት ዕውቅና መስጠት አይሻም!!!

የታጋዮቻችን ዝከራ ይቀጥላል!!!

በሰኔ 1982 ዓም በጎንደር ክፍለ ሓገር በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ሳንኪሳ በተባለው ቦታ በወያኔ ሰራዊት የተያዘው የታወቀው ጸጋዬ ወይን ገ/መድህን ሉጮ እድሜውን በሙሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብት፤ ብልፅግናና ነፃነት ሲታገል የነበረ ሐይወቱን ለዚህ ቅዱስ አላማ ራሱን መስዋእት ያደረገ ጀግና ነው።

ጸጋዬ ያደገው በሸዋ ክ/ሓገር በሚገኘው በዝቋላ አቦ ገዳም ነው። በልጅነቱ መሰራታዊ የሃገራችንን ትምህርት ከመማር አልፎ የቀኔና የአቋቋም ትምህርቱን ለመማር ዕድል አግኝቷል። የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ በሚገኘው የቅዱስ ዮሰፍ ት/ቤት ተከታትሏል። በአማርኛ ቋንቋ ችሎታው ከእኩዮቹ የላቀ ስለነበር በትምህርት ላይ እያለ ለሌሎች ተማሪዎች የአማርኛ መምህር ሆኖ አገልግሏል። ከ ቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ በቋንቋ ትምህርት የመጀመርያ ድግሪውን ካገኘ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች በመምህርነት ሥራ ተሰማርቶ አገልግሏል።

በጓደኞቹ ዘንድ ደብተራው በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው ጸጋዬ ወይን ገ/መድህን ገና በወጣትነት ዘመኑ የህዝብን መከራና ችግር በመረዳቱ የስርአት ለውጥ ለማምጣት የነበረው ፍላጎትና እምነት ከፍተኛ ነበር። በመሆኑም በወቅቱ ተማሪዎች ባደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።የአዲስ አበባ ተማሪዎች ማሕበር (አአዩተማ ‘ኡዝዋ’) ይባል የነበረውን የተማሪዎች ማሕበር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲመሰረት ካደረጉት ግንባር ቀደም ታጋዮች ውስጥ ጸጋዬ ወይን አንዱ ሲሆን በዩኒቨርስቲ ውስጥ በነበረባቸው ዓመታት ውስጥ ተደናቂው የተማሪው ማህበር ጋዜጣ ታገል ( ‘ስትራግል’) የአማርኛ ክፍል አዘጋጅ በመሆንና በተለያዬ ደረጃ የተማሪውን ማሕበር በመሪነት አገልግሏል። በወቅቱ የተማሪው ማሕበር ያካሄዳቸውን ትግሎች በቆራጥነት ከመሩ መካከል ጸጋዬ አንዱ ሲሆን በዚህም በነበረው መንግሥት በተለያዩ ወጣቶች መታሰር ድብደባና ስቃይ ደርሶበታል።

ጸጋዬ ወይን ገ/መድሕን በአገር ቤት ኢሕአፓን ከመሰረቱት ቀደምት አባሎች ውስጥ አንዱ ነው። ጸጋዬ ገና ከመነሻው በአገር ቤት ውስጥ የኢሕአፓ መዋቅር እንዲመሰረትና እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ከመሆኑ ሌላ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋእትነት በመክፈል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብልጽግናና መብት መረጋገጥ ታግሏል። ለተወሰነ ጊዜ በአዲስ አበባ በህቡዕ ከታገለ በኋላ የትጥቅ ትግሉን በማካሄድ ላይ ለነበረው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት (ኢሐአሠ )የፖለቲካ ሃላፊ (ኮሚሣር) በመሆን ወደ አሲምባ(ትግራይ) ሄዶ ለረጂም ዓመታት ታግሏል። በወያኔ እጅ እስከወደቀ ድረስ በኢህአፓ መአከላዊ ኮሚቴ አባልነቱ አመራር በመስጠት ላይ የነበረው ጸጋዬ በበርካታ አምደ ውጊያዎች በመሳተፍ ለሌሎች ሁሉ አርአያ የሆነ ጀግና ታጋይ ነው።

ጸጋዬ ወይን ገ/መድሕን በሥነ ጽሁፍ ችሎታው የታወቀና የተደነቀ ነው። የሥርአትን ምንነትና የለውጥን አስፈላጊነት የሚጠቁሙና የሚቀሰቅሱ በርካታ ድርሰቶችንና ቅኔ አዘል ግጥሞችን ደርሷል። ከነዚህም ውስጥ “ናስተማስሊኪ” ና “ግንባርህን አሳያቸው” የተባሉት ግጥሞችና “ዘውዱን ገልብጬ” በነበረ የተሰኘው ቅኔ ከፍተኛ አድናቆትን ያስገኙና የጸጋዬን የሥነ ጽሁፍ ችሎታ ያስመሰከሩ ሥራዎች ነበሩ። ጸጋዬ “ቱ ኪል ኤ ጄኔሬሽን -ዘ ሬድ ቴረር ኢን ኢትዮጵያ” የተባለውን የባቢሌ ቶላ መፅሓፍ– “አንድ ትውልድ ለመምተር-ቀዩ ሽብር በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉሞታል። ወደ አማርኛ በተተረጎመው መጽሓፍ የጸጋዬ የሥነ ጽሁፍ ችሎታ ምን ያህል የመጠቀ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ጸጋዬ ከመታሠሩ በፊት ዲሞክራሲያ የተባለውን የኢህአፓን ልሳንና ሌሎች የፓርቲው ጽሑፎችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረገ ከመሂኑ በላይ ጸጋዬ ከጻፋቸው የዲሞክራሲያ እትሞች መካከል በቋንቋ ይዘታቸውና በቀስቃሽነታቸው የሚደነቁ በርካታ ናቸው።

ጸጋዬ በጓደኞቹ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ ሌላ ብልህ፤ታታሪና ቆራጥ የጀመረውን ዳር ሳያደርስ የማይሰለቸውና የማይታክተው ራሱን የማያስቀድምና ልታይ ልታይ የማይል ቅንና ትሁት ሰው ነው። ጸጋዬ በሌላ በኩል ተጫዋችና ቀልደኛ፤ ከትንሽ ትልቁ ተግባብቶ የሚሰራ ጓድ ነበር።

በ 1982 ዓም የወያኔ ጦር በጎንደር ክ/ሓገር በኢህአፓ ሠራዊት–በኢሕአሠ ላይ በከፈተው ጥቃት ጸጋዬ ወይን ግ/መድሕን፤ በለጠ አምሓ፤ ስጦታው ሁሴን፤ይስሃቅ ደብረጽዮን፤ ተክላይ ግ/ሥላሴ፤ ኅጎስ በዛብህ አበራ ደሳለኝና ሌሎች በወያኔ እጅ ወድቀው ከዝያ ጊዜ ጀምሮ የደረሱበት ሳይታወቅ በወያኔ እሥር ቤት በመሰቃዬት ላይ ይገኛሉ።

ሓገር ወዳድ የሆኑ ዜጎች ሁሉ ጸጋዬና ጓዶቹን እንዲሁም በሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞች ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እስኪፈቱ ትግላችን ይቀጥላል።

ደብተራው ለትግሉ የከፈለው መስዋእትነትና ፅኑ ታጋይነት በአሁኑ ሰአት ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ላለው ወጣት ትውልድ አርአያና ምሳሌ ነው። በጣም እንኮራበታለን።

የጠፉ፤ ያለፉ፤ ህይወታቸውን ለትግሉ የሰጡ ኢንዲሁም የተሰዉ ጓዶቻችንን የማስታወስ ብሎም የቆሙለትን አላማ ግብ የማድረስ ሃላፊነት ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው!!!!

ወያኔ፤ ወያኔነትን፤ ጽንፈኝነትን፤ጎጠኝነትን፤ በአንድነት እንዋጋ!! አንድነት ሃይል ነው !!!

ኢትዮጵያዊነት ምንግዜም አቸናፊ ነው!!!!!

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!

“ግንባርህን አሳያቸው” የሚለውን የደብተራውን ለትግል አነቃቂ ግጥም ጋብዣችኋለሁ!!! ለማዳመጥ ሊንኩን ተጫኑ!!!

Categories: ሬዲዮ ዘመራ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s