ሬዲዮ ዘመራ

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ፕሮግራም እንዲታገድ ፓትርያርኩ ያቀረቡት አጀንዳ የቋሚ ሲኖዶሱን ተቀባይነት አላገኘም

ከውጉዙ የአሰግድ ሣህሉ ቴሌቭዥን ጋራ በማጃመል፣ “እንዲታገድ ይወሰነልኝ፤” ሲሉ ጠየቁ፤“ውጉዙንና ሕጋዊውን እንዴት በአንድነት ያቀርባሉ?” በሚል አጀንዳቸው ተቃውሞ ገጠመው፤የማኅበሩ ተወካዮች ተጠርተው እንዲያብራሩ አባቶች ሐሳብ ቢያቀርቡም፣ ፈቃደኛ አልኾኑም፤“እንግዲያውስ ዝም ብለን አናግድም፤ ለቤተ ክርስቲያን አደጋ አለው፤” ብሎ ቋሚ ሲኖዶሱ ሳይቀበለው ቀረ፤

የሰርጎ ገብ ፀራውያን ውትወታ በቋሚ ሲኖዶሱ ቢወድቅም፣ በፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ቀጠለ፤አባቶች፣ ማኅበሩ በኢኦተቤ – ቴቪ ጣቢያ እንዲያገለግል ፍላጎት እንዳላቸው በአጽንዖት ገለጹ፤ማኅበሩም፣ ጣቢያውን በሞያተኛና በቴክኖሎጂ ለማጠናከርና በጋራ ለመሥራት አቋሙን አስረገጠ፤21740330_1486480954766032_3684803849824325292_n

የዓመቱ መባቻ የአሌፍ ጣቢያ ሥርጭቱ፣ በየሳምንቱ ቅዳሜ ሠርክና እሑድ ረፋድ ይቀጥላል፡፡
†††

ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች የማስፋፋት ደንባዊ ዓላማና ተግባር ያለው ማኅበረ ቅዱሳን፣ በዓመቱ መባቻ፣ በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ የጀመረው የሙከራ ሥርጭት እንዲታገድ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለቋሚ ሲኖዶስ ያቀረቡት አጀንዳ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት፣ “ፕሮግራሙን አላውቀውም፤” ሲል ባለፈው ሳምንት ሰኞ ለፓትርያርኩ ደብዳቤ መጻፉን ተከትሎ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ “የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ተጥሷል፤ ፕሮግራሙ እንዲታገድ ይወሰነልኝ፤” በማለት ቢጠይቁም አጀንዳው ተቀባይነት ሳያገኝ ያለውሳኔ መቋጨቱ ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኑፋቄው ተወግዞ የተለየው አሰግድ ሣህሉ፣ “ቃለ ዐዋዲ” በሚለው የቤተ ክርስቲያናችን ደንቦች ስያሜ የቀጠለው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙም ርምጃ እንዲወሰድበት የጠየቁት ፓትርያርኩ፤ “ማኅበረ ቅዱሳንም የቴሌቭዥን ጣቢያ ከፍቷል፤ የሲኖዶሱን ውሳኔ የጣሰ በመኾኑ መዘጋት አለበት፤ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደረግ የእግድ ደብዳቤ ይጻፍልኝ፤” የሚል አጀንዳ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡

መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ የተወገዘው፣ ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳይሰጠው ከቤተ ክርስቲያን ውጭ አዳራሽ ተከራይቶ፣ ትምህርተ መለኰትን፣ ሥርዓትንና ቀኖናን እያፋለሰ ምእመናንን በመቀሠጡ እንደኾነ ያወሱት የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት፤ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደርያ ደንብ በሚጠራበት “ቃለ ዐዋዲ” ስም የሚያሠራጨው ፕሮግራሙም ርምጃ እንዲወሰድበት ቅዱስነታቸው በአጀንዳው ያቀረቡትን ሐሳብ ደግፈዋል፡፡

ኾኖም፣ ማኅበረ ቅዱሳንም የጀመረው የቴሌቭዥን ፕሮግራም መዘጋት አለበት፤ ሲሉ ሥርጭቱ እንዲታገድ አጃምለው ማቅረባቸውን የቋሚ ሲኖዶሱ አባቶች ተቃውመዋል፡፡ “በኑፋቄው ተወግዞ የተለየ ግለሰብን ድርጊት፣ እንዴት ከሕጋዊው ማኅበር አገልግሎት ጋራ በአንድነት ያቀርባሉ? ምን አገናኛቸው?” ሲሉ ጠይቀዋቸዋል፡፡ “ጉዳዩ አብሮ መቅረብ የለበትም፤ ማኅበሩ ዕውቅና የሰጠነው ሕጋዊ ተቋም ነው፤ በእኛው ሥር ያሉ ናቸው፤ የእኛው ልጆች ናቸው፤” ያሉት ብፁዓን አባቶች፣ በደንቡ መሠረት ከድርጅቱ የአየር ሰዓት እንዲሰጠው ቢጠይቅም አዎንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ውሳኔው ያገዳቸው ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች፥ ቤተ ክርስቲያን በማታውቀው ኹኔታ የቤተ ክርስቲያንን ፈቃድ ሳያገኙ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች በስሟ እየነገዱ ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ እንደኾነ በመጥቀስ፣ ውሳኔው ማኅበሩን እንደማይመለከት አስረድተዋል፡፡

ይህም ኾኖ፣ ፓትርያርኩ ባቀረቡት አጀንዳ ላይ መወያየት የሚቻለው፣ በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ ስለተጀመረው ሥርጭት የማኅበሩ ተወካዮች ተጠርተው፣ ለምንና እንዴት እንደሔዱ እንዲጠየቁና አጠቃላይ ሒደቱን እንዲያብራሩ ከተደረገ በኋላ ብቻ እንደኾነ የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት በአንድ ድምፅ መናገራቸው ተመልክቷል፡፡

ይህ ባልኾነበት፣ ፓትርያርኩ እንደጠየቁት በዘፈቀደ የእገዳ ውሳኔ ቢተላለፍ፥ ተቀባይነት የማይኖረው ብቻ ሳይኾን፣ ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ ሊቀሰቅስና ቤተ ክርስቲያኒቱንም ሊከፋፍል እንደሚችል በመጥቀስ የሚያስከትለውን ቀውስ ለቅዱስነታቸው በግልጽ ለማስረዳት ጥረት እንደተደረገ ተጠቁሟል፤ “አደጋው ይታይዋት፤” ሲሉም አሳስበዋቸዋል፡፡

“ብዙ ሀብት አላቸው እንጅ ጥቂቶች ናቸው፤” ሲሉ ማሳሰቢያውን ያጣጣሉት ፓትርያርኩ በበኩላቸው፣ “ያው እንግድህ ተከፍለናል፤ ኹለት ዓይነት ሐሳብ ነው ያለው፤ ምን ይደረጋል እንግዲህ፤” በማለት አቋማቸውን ለማጽናት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ በዚኽ መልኩ ውይይት ሳይደረግበት የታለፈው የፓትርያርኩ አጀንዳ፣ የቋሚ ሲኖዶሱን ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ታውቋል፡፡

ከዛሬው የቋሚ ሲኖዶሱ ቀደም ሲል፣ ትላንት በመንበረ ፓትርያርኩ የስብሰባ አዳራሽ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች፣ የዐዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሰንበት ት/ቤቶች መዘምራን በተገኙበት፣ የዐዲስ ዓመት እንኳን አደረስዎት መርሐ ግብር፣ “ተቀጽላ አያስፈልግም፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንዲት ናት፤ ሌላ ቤተ ክርስቲያን የለም፤ አገልግሎታችንም አንድ ዓይነት ብቻ ነው መኾን ያለበት፤” በማለት መልእክት አስተላልፈው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ከዚሁ የፓትርያርኩ መልእክት ቀደም ሲል፣ በንባብ የተሰማው የዐዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መግለጫ፣ በመናፍቁ አሰግድ ሣህሉና መሰሎቹ ላይ እየተወሰደ ያለውን ርምጃ የሚደግፍና በቀጣይ መወሰድ ያለበትን የሚጠቁም ቢኾንም፣ ፓትርያርኩ፣ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው መተዳዳርያ ደንቡ መሠረት በሚያሠራጨው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙ ላይ ማተኮራቸው በብዙዎች ዘንድ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል፡፡

ያም ኾኖ፣ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ አንዳንድ የቦርድ አባላት(ሰብሳቢውን ብፁዕ አቡነ ማርቆስንና ምክትላቸውን ንቡረ እድ ኤልያስን) እንዲሁም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በወሰዱት የክፋት ተነሣሽነት፣ ለፓትርያርኩ የተጻፈውን ደብዳቤ ተከትሎ፣ ሰርጎ ፀራውያን፣ የቋሚ ሲኖዶሱን አባላት በፀረ ማኅበረ ቅዱሳን አቋም ለማግባባት ያደረጉት ሰሞናዊ ሽር ጉድ ሳይዝላቸው እንደቀረ በዛሬው ውሳኔ ተጋልጧል፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ “ለቤተ ክርስቲያን እንጅ ለማኅበሩ ድጋፋችሁን ማቆም አለባችሁ፤” እያሉ ሥርጭቱ እንዲታገድ የሚጠይቅ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል፣ የዛሬውን የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ተከትሎ የማኅበሩን አመራሮች ያነጋገሩ ብፁዓን አባቶች፣ ፍላጎታቸው፣ ማኅበሩ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተመልሶ እንዲያገልግል መኾኑን ገልጸዋል፤ “እዚህ እንዲሰጣችኹና እንድታስተምሩ ነው የምንፈልገው፤” ብለዋል፡፡ ከጣቢያው የአየር ሰዓት በተደጋጋሚ መጠየቅ ብቻ ሳይኾን፣ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ለመደገፍና ለማጠናከር በደብዳቤ ጭምር እንደለመነ ያወሱት አመራሮቹ፣ ማኅበሩ የጠየቀው የአየር ሰዓት ከተፈደለት ተመልሶ ለመጠቀም ዝግጁ መኾኑን ላነገሯቸው ብፁዓን አባቶች አረጋግጠዋል፡፡

እስከዚያው ድረስ፣ በዐዲሱ ዓመት መባቻ በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ የጀመረውን የሙከራ ሥርጭት በመቀጠል፣ በየሳምንቱ፤

ቅዳሜ ሠርክ፡- ከቀኑ 11፡30 እስከ ምሽት 2፡30
እሑድ ረፋድ፡- ከ4፡30 እስከ 8፡00
መርሐ ግብሮቹን እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል፡፡ ከትላንት በስቲያ፣ መስከረም ቀን ረፋድ 4፡00 ላይ ሥርጭቱ ከጀመረ በኋላ በቴክኒክ እክል ተቋርጦ የነበረ ቢኾንም፣ ከቀትር በኋላ ቀጥሎ መተላለፉን ጨምሮ ገልጿል፡፡

Categories: ሬዲዮ ዘመራ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s