ዜና

ንብረትነቱ የም/ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ከሆነው ሚሽከን ኮሌጅ ተምረው የተመረቁ ተማሪዎች ከስራ ገበታቸው እየታገዱ ነው ተባለ

ምስል ከፋይል የአገሪቱን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገጠመው የጥራት ጉድለት በአገዛዙ ባለሥልጣናት ጭምር መተቸት ጀምሯል። ደመቀ መኮንን የህወሃት አገዛዝ ለይስሙላ ካስቀመጣቸው ጠቅላይ ሚንስትሮች አንዱ የሆነው ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚንስትር በነበረበት ወቅት በሸርክና ያቋቋመው ሚሸከን ኮሌጅ በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች፤ በማኔጅምንት ፣ በአካውንቲንግ እና በኢኮኖሚክስ ዘርፎች ላለፉት 5 አመታት አስተምሮ በሰርተፍኬት እና በመጀመሪያ ዲግሪ ካስመረቃቸው ከ15000 በላይ…

 

የአገሪቱን  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገጠመው የጥራት ጉድለት በአገዛዙ ባለሥልጣናት ጭምር መተቸት ጀምሯል።

ደመቀ መኮንን
የህወሃት አገዛዝ ለይስሙላ ካስቀመጣቸው ጠቅላይ ሚንስትሮች አንዱ የሆነው ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚንስትር በነበረበት ወቅት በሸርክና ያቋቋመው ሚሸከን ኮሌጅ በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች፤ በማኔጅምንት ፣ በአካውንቲንግ እና በኢኮኖሚክስ ዘርፎች ላለፉት 5 አመታት አስተምሮ በሰርተፍኬት እና በመጀመሪያ ዲግሪ ካስመረቃቸው ከ15000 በላይ ተመራቂዎች መካከል የ4378ቱ የትምህርት መረጃ ውድቅ መደረጉን ለትንሳኤ ሬዲዮ ከደረሰው  መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የትምህርት መረጃቸው ውድቅ የተደረገባቸው እነዚህ 4378 ተመራቂዎች በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ መንግሥት መሥሪያቤቶችና ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው ሲያገለግሉ እና በሚሠሩበት የሥራ መደብ የተለያየ የደረጃ ዕድገት ሲሰጣቸው  የቆዩ እንደሆነም ታውቋል። በዚህም የተነሳ የሰዎቹ ትምህርት መረጃ ውድቅ መደረጉና  ከሥራ ገበታቸው መባረር ካለፈው አመት ጀምሮ በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ የአመቱ የፌደራል ጉዳዩች የስራ አመራር ቦርድ ገልፅዋል፡፡
ቦርዱ ፡- የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ ዝቅተኛና የሀገሪቱ የእድገት ግብና ፍላጎት የሚያሟላ የተማረ ትውልድ ለመፍጠር የማያስችል በመሆኑ ሀላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንዳልቻለ የመንግስት ጉዳዩች የስራ አመራር ቦርድ ገልጿል፡፡
ቦርዱ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ጥራት ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ግምገማ በተመለከተ ከ2004-2009 ዓ.ም  ያተኮረ ግምገማ  አድርጎ ፤ የትምህርት ጥራት አግባብነትን ከማረጋገጥ አኳያ ኤጀንሲው ድክመት ያሳየባቸውን ተግባራት በዝርዘር ማቅረቡም ታውቆአል። ቦርዱ አቅርቦአል በተባለው ዝርዝር ውስጥ ኤጄንሲው የትምህርት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ አለመላኩ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጧቸው ትምህርቶችና ስልጠናዎች ከሀገሪቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎት እንዲሁም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋር የተገናዘቡ ስለመሆናቸውና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚፈለጉ ብቁ ተመራቂ ተማሪዎችን ማፍራት ስለመቻላቸው ማረጋገጥ ሲገባው ተቋማቱ እነዚህን ሀላፊነቶች እንዲወጡ የሚያስገድድበት ህጋዊ መነሻ የለውም በሚል ሰበብ ሀላፊነቱን አለመወጣቱ፣ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀረጹት የትምህርት ፕሮግራሞች ተግባራዊ መደረጋቸውን አለማረጋገጡ፣ ካሪከለሙ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርቶች መጠናቀቃቸውን የሚያረጋግጥበት ስርዓት የሌለው መሆኑ እንዲሁም ተመራቂዎች ተፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው መመረቃቸውን የማያረጋግጥበት የሙያ ብቃት ምዘና ስርዐት ያልዘረጋ መሆኑ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለተማሪዎች ጥቅም የሚውሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የማደሪያ፣ የመመገቢያ ቁሳቁሶች፣ ግብአቶችና አገልግሎቶች እንዲሁም ለመምህራን የሚውሉ አገልግሎቶች በሚፈለገው ሁኔታ ያልተሟሉ፣ ያልተመጣጠኑ፣ ጥራታቸውን ያልጠበቁና ለደህንነት ስጋት የሚፈጥሩ ሆነው መገኘታቸውንና አገልግሎት መስጠታቸውን መከታተል አለመቻሉ፣ አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገነቡም ሆነ ነባሮቹ ሲስፋፉ ግንባታዎች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ታሳቢ ስለማድረጋቸው የማይከታተል መሆኑ፣ ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን በመሚመዝኑበት አሰራር ውስጥ መምህራኑ የሚያቀርቡት ቅሬታ በአፋጣኝና በጥንቃቄ መፍትሄ የሚያገኝበት ስርአት መፈጠሩን የሚያረጋግጥበት የአሰራር ስርዐት የሌለው መሆኑ እንዲሁም የግልም ሆነ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የተመለከተ መረጃ ያልያዘና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ወቅቱን የጠበቀና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ ስርአት ያልዘረጋ መሆኑ ተጠቅሰዋል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሙልዬ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ኤጀንሲው የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ቢያዘጋጅም አለመላኩ ስህተት መሆኑን፣  ነገር ግን ስራዎቹ አሁን ኤጀንሲው ባለው አደረጃጀት ሊፈጸሙ የማይችሉ በመሆኑ የአሰራር ስርአት በመዘርጋት ላይ ማተኮሩን፣ ከአደረጃጀት ጥበትና ከመዋቅር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ጥናትና ምርምር በማካሄድ ግኝትን መሰረት አድርጎ ስትራቴጂ የሚቀርጽና ስርአት የሚነድፍ አደረጃጀት ባለመኖሩ የተፈጠረውን ትልቅ ክፍተት ለመሙላት በመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ የጥናትና ምርምር ስታንዳርዳይዜሽንና አለም አቀፍ ተሞክሮ ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም እንዲሁም የትምህርት ተቋማቱን እንቅስቃሴዎችን ለመከታተልና ለመደገፍም የተቋማት ኢንስፔክሽን የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲቋቋሙ መደረጉን፣ ከዚህ ውጪ ግን በግምገማው የቀረቡት እያንዳንዱን ችግሮች በየዩኒቨርስቲዎቹ እየተከታተሉ እንዲፈቱ ለማድረግ ቀርቶ በፕሮግራም የተያዙ ኦዲቶችን እንኳ በአግባቡ ለማከናወን ኤጀንሲው አቅም እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
ሌሎች የኤጀንሲው ኃላፊዎችም ኦጀንሲው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው የትምህርት ጥራት ኦዲት መሰረት ማስተካከያ እንዲደረግ ከመንገር ባለፈ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ የሚያስገድድበት አሰራር የለም ብለዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የትምህርት ተቋማት ሲገነቡና ወደ ስራ ሲገቡ በኤጀንሲውና በትምህርት ሚኒስቴር መሀከል ቅንጅት አለመኖሩን፣ ኤጀንሲው የትምህርት ጥራትና አግባብነትን የማረጋገጥ ስራውንም ሆነ የእውቅና አሰጣጡን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል በቂ ሰው ሀይል የሌለው መሆኑን፣ የርቀት ትምህርት መርሀ ግብር የሚሰጡትን የመንግስት የትምህርት ተቋማትን በሙሉ ባለው አቅም በልዩ ሁኔታ ኤጀንሲው እየገመገመና ፈቃድ እየሰጠ እንደሆነ ሆኖም ግን መደበኛ መርሀ ግብር ላይ ያሉትን በመገምገም እውቅና በመስጠት ላይ ግን በአቅም ውስንነት ምክንያት እንዳልሄደበት እንዲሁም ኤጀንሲው ራሱን ለሚመለከታቸው አካላት በቅርበት እንዳላስተዋወቀና መግባባት ላይ እንዳልደረሰ የስራ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡
ኤጀንሲው አሁን ባለበት ቁመና የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ እድገቷ የምትፈልገውን ብቁ የሰው ሀይል ለማምረት የትምህርት ጥራትና አግባብነትን የማረጋገጥ ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ባለመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ከአምስት አመት በፊት በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ላይ ኦዲት ተደርጎ በርካታ ችግሮች እንደተገኙ በማስታወስ በእነዚህ ላይም ምንም አይነት እርማት እንዳልተወሰደ ገልጸዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን አዲስ በሚገነቡ ዩኒቨርስቲዎችም ሆነ በነባር የትምህርት ተቋማት የሚከናወን የማስፋፊያ ግንባታ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ፍላጎትና መብት ትኩረት መሰጠቱን ማረጋገጥ እንደሚገባው፣ ለዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ጥራት መሟላት አስፈላጊ ግብአቶች በጎንዮሽ ዘዴዎችም ሆነ በተራዘመ አግባብ መሟላታቸውን የመቆጣጠር ስልጣን አለኝ ብሎ ስልጣኑን በቅንጅትም ሆነ በተናጠል መጠቀም እንደሚጠበቅበት፣ ተቋሙ ስለተልእኮና ስለሀላፊነቱ ራሱን ለህብረተሰቡም ሆነ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅና በዚህም የሚገኙ ግብዐቶችን መጠቀም እንደሚያሻው፣ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ የሚያጋጥሙ ከኤጀንሲው አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ሆነ ለከፍተኛ ትምህርት ቋሚ ኮሚቴ በማሳወቅ ተጠያቂነት እንዲመጣ መስራት እንደሚገባው፣ በተቋሙ ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር የተቋሙን አቅም የሚጎዳና ተልዕኮውን እንዳይወጣ የሚያደርግ ዋነኛ ችግር በመሆኑ በአመለካከትና በአቅም የተሟላ ፈጻሚ ለመፍጠር በመ/ቤቱ የሰው ሀይል ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባው እንዲሁም ከባለድርሻ አካላትና ከህዝብ ክንፉ ጋር ያለውን ትስስርና ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ satenaw.com

Categories: ዜና

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s